tg-me.com/Getem_lemitemaw/629
Last Update:
💚💛❤️አድዋ💚💛❤️
.
.
እንዴት! ያውም አድዋን!?
(በድሉ ዋቅጅራ)
.
ምነው!?
አድዋን ያህል ታቦት!
ነጻነትን ያህል ጽዋ!
ምነው አጣ፣ አንጋሽ - ደጋሽ፣
የጀግና አባቱን፣ ድል ወራሽ?
ምነው?
.
ምነው?
ምነው! ጭር አለ ቀዬው፣ ዳዋ ዋጠው ደብሩ፤
ፎካሪ ናፈቀ ፈፋው፣ ሸላይ ጠፋ ባገሩ፡፡
ምነው?
.
ምነው?
በደም ቀለም፣ በአጥንት ብእር የተጻፈ ገድል፤
የጥቁር ህዝቦች፣ የነጻነት ውል፤
አድዋን ያህል ድል?
ምነው!?
.
ምነው!?
እንደመጥበትን ልቦና፣ እንናገርበትን ልሳን፣
አንከበርበትን ግርማ፣ እንከብድበት ሚዛን፣
ምነው! . . . . ያውም አድዋን!?
.
ምነው!?
በጎሰኝነት ችካል፣ በየጎጡ ጋጥ ታስረን፤
‹‹አድዋ!›› ማለት ከበደን፤
‹‹ኢትዮጵያ!›› ማለት ሸከከን፡፡
ባንባረክ ልንባርከው፣ ቅርጫ ʽናረገው አማረን፡፡
የአባቶቻችን ድል አሳከከን፤
ለትርክት አንደበት አጠረን!
ጀግንነትን አንውረስ - እንፍራ፣ እዳ አለው፣
ስንቀል ይከብዳል፤
ጀግንነት ጣር አለው ይቅር፣
እንዴት ድል መውረስ ያቅታል!?
.
ምንስ ድንቁርና ቢጎራበተን፤
ጎሰኝነት ቢያባትተን፤
እንዴት ድል መውረስ ያቅተን!
ያውም አድዋን! ከሀገር፣ ከሰንደቅ፣ ከነጻነትም በላይ፤
የሰው መሆንን ማተብ፣ የ‹‹ሳቬጅ›› ተረት ተርትን ስራይ፤
የአፍሪካን የነጻነት አዋይ፤
እንዴት!
.
ኧረ ወገኔ ውሉን ስቷል፤
አድዋ ተራራ መስሎታል!
ሸንሽኖ ሊከፋፈለው፣ ኮረብታ ሊያደርገው አምሮታል፡፡
አድዋ የአንድ ቀን ውሎ፣ አድዋ ተራራ መስሎታል፡፡
.
መንፈስ እኮ ነው አድዋ፣ . . . .
ፈለግ - ለመንገዳችን፣ ለታሪካችን - ልሳን፤
ዙፋን - የነጻነታችን፣ የአብሮነታችን ቁርባን፤
የመረዳዳት ፍሬ፣ የኢትዮጵያዊነት መልህቅ፤
የደገፈን - እንዳንወድቅ፤
ያጸናን - እንዳንዋዥቅ፡፡
እንዳንፈርስ ያጠነከረን፣ . . .
እንዳንጎድል - ቀድሞ የሰፈረን፡፡
. . . . . ምነው ዘመን አወረን!?
.
አድዋ እንደሁ መንፈስ ነው!
እንኳን ጎጥ - ሀገር ያልቻለው፤
ጽናት - አህጉር የጠበበው፤
አይገድቡት - ይፈሳል፤
አያቅቡት - ይዳረሳል፡፡
.
ታዲያ ምነው!?
ምንስ ድንቁርና ቢጎራበተን፤
ጎሰኝነት ቢያባትተን፤
እንዴት ድል መውረስ ያቅተን!
ያውም አድዋን!
-------------
የካቲት 23፣ 2009፤ አዲስ አበባ፡፡
ለመላው የጥቁር ህዝቦች ኩራት ለሆነው ለታላቁ የአድዋ ድል 125ኛ ዓመት የመታሰቢያ ክብረ በዓል እንኳን በሰላም አደረሳችሁ !አደረሰን ።🙏
💚💛❤️💚💛❤️💚💛❤️💚💛❤️
@Getemlemitemaw
@Getem_lemitemaw
BY ግጥም ለሚጠማዉ
Warning: Undefined variable $i in /var/www/tg-me/post.php on line 280
Share with your friend now:
tg-me.com/Getem_lemitemaw/629