tg-me.com/wegoch/5214
Last Update:
"የተኛህበትን ሳታመላክተኝ
ስታዞረኝ አደርክ ስታንከራትተኝ።"
.
.
.
ሄዷል። ድንገት። ድንገቴው ለኔ ነው። የት እንደሄደ፣ ለምን እንደሄደ ምኑም አልገባኝም። ሳይገባኝ ልፈልገው ጣርኩ። እየኖረ እንዴት ይሄዳል ሰው? መኖርም መሄድም እንዴት በኩል አፍታ ይገለጣሉ? ባንድ ሰውነት ላይ እኩል? ስሄድ ጭልጥ፣ ግንጥል ብሎ መሄድን፤ ስኖር ጥግት፣ ጥብቅ ብዬ መኖርን ነው የማውቅና ግራ ገባኝ።
አስራ አምስት አመታት የጎነጎነው በሱ በኩል ለቆት ኖሮ ያለመልኩ ብትንትን፣ ጭብርር፣ ስብርብር አለ። ልብና አይምሮዬ ላይ አለ እና ሄደ ተደራረበ። እንኖራለን እያልኩ መኖርን ስሸምን መለያዬት ተከናነብኩ። ደህና መሆኔን፣ ሰላሜን፣ ቀጥና ቀና ብዬ መራመዴን የሄደ ቀን ይዞት ሄደ። ቀነጣጥሶኝ። እኔ እኔን አልሰማ አለች። አይቻት የማላውቃት ሌላ ሴትዮ ተፈለቀቀች። ያለመድኳትን ሴት ተሸከምኩ። የጎበጠች፣ አንገቷን የደፋች፣ ሰው የፈራች፣ ችላ ብትጠጋም የማትላተም። መውደድ የሚያስበረግጋት። መጠጋት እንዳያፍነከንካት በዛው አፍታ የመለየት ሃሳብ የሚያስፈራት ፈሪ ተፈጠረች።
መሄዱን ሂድ ግን እኔን መልስልኝ አልኩት የሆነ ቀን ሳወራው። ሌላ አላለም፣ ሙቭ ኦን እናድርግ ለሁለታችንም እሱ ነው የሚሻለን አለኝ። ቀድሞኝ ትቶኝ ተሻግሯል አውቃለሁ። እኔ ግን ወዴት እንደምሻገር ማወቅ ተሳነኝ። ድልድዬን ሰብረኸዋልኮ ልለው ነበር ይከፋዋል ብዬ ዝም አልኩ።
"እህህ ጠዋት ማታ እህህ ሌሊት
ይሄ ሆኗል ትርፌ ካንተ ያገኘሁት"
.
.
.
ሁሉም ይሄዳልኮ። መሄድ ሰውኛ ነው ማንም የሚሄደው። ልንሄድ ነው የመጣነው። የሚለዬው አካሄዱ ነው። የሄደው ሰው ዓይነት ነው። የቀረብን፣ ያጣነው ነገር ነው። ለዛ ነው የከበደኝ። ለዛ ነው እንዳዲስ ጉዳይ እያደር መሄዱን የማያምን ልቤ። ለዚሁ ነው እረሳሁት ባልኩ ማግስት ከሲናፍቀኝ ስሜት ጋር ግብ ግብ ገጥሜ ከራሴ የምጣላ።
ስነቃ ከሄደበት አፍታ መገረምና አለማመን ጋር እነቃለሁ። እውነት ሄዷል? በእህህታ ሳብሰለስል እውልና እንቅልፍ ዓይኔን ከመክደኑ ፊት በህቅታ እንዲወጣልኝ ከእንባዬ ጋር እንዳንገዋለልኩት ሽፋሽፍቴ እንደራሰ እንቅልፍ ይጥለኛል። ስነቃም ሃሳቤ ውስጥ ይኖራል። እንዲያ ሆነ የኑሮዬ ድግግሞሹ። በሆነ ባልሆነው ተነጫነጭኩ። ራሴ ላይ፣ ሃሳቤ ላይ፣ እቅዴ ላይ፣ ህልሜ ላይ፣ ቁጭቴ ላይ፣ ትላንቴ ላይ፣ ዛሬዬ ላይ፣ ነገዬ ላይ፣ ህይወት ላይ፣ እግዜሩ ላይ።
ለምን እንደሄደ፣ ለምን እንደበቃሁት፣ ባይለውም ለምን እንደጠላኝ እንዲገባኝ ስዳክር ስድስት አመታት ተሻገርኩ ከህመሜ ጋር። እሱ እንዳለውም ተሻግሯል። አስራአምስት አመት የቆዬ አብሮነታችንን እንደዋዛ ጥሎ፣ ከራሱ ጋር ከነፍሱ ጋር ይደልቃል፣ በዝምታ።
በነዚህ ሁሉ ጊዜያት ለምን ግን እለዋለሁ እግዜሩን። በአካል የተገለጠ ሰው ሲያምረኝ። የሚያወራኝ፣ ምኑንም ምኑንም የሚቀባጥርልኝ። ያለመስመር፣ ያለመጠንቀቅ ሁሉን። ሳቅ የሚወልድልኝ። ወሬ አልቆብንም ዝም ብለን የምንቆይ። ዝምታችንም የሚያወራ። እንደገና የምንቀጥል። እሱን የሚያስረሳኝ። ሰው በሰው ነው የሚረሳው ይሉ የለ? የምረሳበትንም ባይሆን የሚተካልኝን ሰው አምጣው እንጂ እያልኩ ንጭንጭ እግዜሩ ላይ። ከትላንቴ ተጣብቄ አረጀሁኮ፣ አዲስ ዛሬ ስጠኝ እንጂ ንትርክ። ለምን እኔ ማንም የሌለኝ? ለምን እኔ ፍቅሬን የተነጠኩ? ለምን እኔን ከሰው አጥንት አልፈለቀከኝም? ከሰው ግራ ጎን አልሸለቀከኝም? ናፍቀሽኛል መባል አያምረኝም? አውሪኝ ትንሽ አትሂጂ መባል አይጎበኘኝም? ለምን እኔ? መች ነው የኔ ወረፋ? መች ነው ልቤ የሚሞላ ዳግም?
"ስሄድ ስሄድ ውዬ ስሄድ ስሄድ ነጋ
ጅብ አይበላም ብዬ የናፋቂን ስጋ"
.
.
.
ዛሬ ሌሊት በጣም ናፈቅኸኝ። ሁሌም ነው የምትናፍቀኝ፣ ሄዷል በቃ ብዬ አልተውኩህም። ትቶኛል በቃ ብዬ አልተቀየምኩህም። ትናፍቀኛለህ። እያለህ እንደምናደርገው በእኩለ ሌሊት ንፋስ ስልክ ጎዳና ላይ እንራመድ ብዬ ወጣሁ። አብረኸኝ ነበርክ። እያወራኸኝ፣ እያሳቅኸኝ፣ ያቺን ምላስህን አውጥተህ ትልልቅ ዓይንህን ለማጥበብ የምትታገልባትን ፊትህን እያሳየኸኝ። እየተራመድን ትተኸኝ ሮጥክ ልይዝህ ተከተልኩህ። አጥሩ የፈረሰው ዮሴፍ ቤተክርስቲያን ግቢ ውስጥ ተከትዬ ዘልዬ ገባሁ።
" እስኪ እናንተ ተኙ እኔ ስራ አለብኝ
ግንብ እገነባለሁ ፍቅር ተንዶብኝ"
.
.
.
አቅፌህ ካሸለብኩበት የጎረነነ ድምጽ ቀሰቀሰኝ። 'የኔ እህት እባክሽ ትለከፊያለሽ በዚህ ሌሊት አትምጪ፣ ብርዱም አይቻልም' መቃብር የሚቆፍር ጎልማሳ ቁልቁል እየተመለከተኝ። አያውቅም ቤቴ አንተ እንደሆንክ። አያውቅም የተናደ ፍቅሬን እዚህ እየመጣሁ ልገነባ እንደምጥር። አያውቅም ማንም እንደሌለኝ። አያውቅም ልክፍቴ ወዳንተ መምጣት እንደሆነ። አያውቅም የሚሞቀኝ እዚህ እንደሆነ። አያውቅም ምንም። ናፍቀኸኛል......
@wegoch
@wegoch
@paappii
By Martha Haileyesus
BY ወግ ብቻ
Warning: Undefined variable $i in /var/www/tg-me/post.php on line 280
Share with your friend now:
tg-me.com/wegoch/5214