tg-me.com/yetenantun_lenege/345
Last Update:
የአራቱ ወንጌላት መልእክትና ይዘት፦
አራቱ ወንጌላት በየክፍላቸው መዝግበው የያዙት ስለአምላካችን ጌታችንና መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ታሪክና ሥራ ነው። ሁሉም ይህንኑ ታሪክና ሥራ ቢናገሩም እያንዳንዳቸው ከሌሎቹ የሚለዩበት የአመዘጋገብና ያገላለጽ ሁኔታ አለ። ለምሳሌው ያህል ለመጥቀስ በአንዱ የወንጌል ክፍል ተመዝግበው በሦስቱ ወንጌላት ላይ ያልተመዘገቡና የማይገኙ፣ በሁለቱ ወንጌላት ተመዝግበው በተቀሩት በሁለቱ ላይ የማይገኙ፣ እንዲሁም በሦስቱ ወንጌላት ተመዝግበው በቀሪው አንድ ላይ ያልተመዘገቡና የማይገኙ አንዳንድ የጌታ ታሪኮችና ሥራዎች ስለሚገኙ ነው። ይህንን ጠንቅቆ ለመረዳት በእያንዳንዱ መጽሐፍት ግርጌ ባለው የኅዳግ ማመሳከሪያ በመጠቀም ፬ቱንም ወንጌላት ማነጻጸር ይቻላል።
የማቴዎስ፣ የማርቆስና የሉቃስ ወንጌላት <ሲኖፕቲክ> ተብለው ይጠራሉ።
<ሲኖፕቲክ> ማለት ተመሳሳይ ማለት ሲሆን ቃሉ የግሪክ ቃል ነው። ሦስቱ ወንጌላት በይዞታቸው በብዙ ክፍል ስለሚመሳሰሉ ይህንን መመሳሰላቸውን ለማስረዳት የተሰጣቸው ስያሜ ነው። ምክንያቱም ሦስቱም ወንጌላት አንድ ዓይነት መልእክታትን ጽፈው ይገኛሉና። ምንም እንኳን የጌታ ተመሳሳይ ታሪክና ሥራ በ፫ቱ ወንጌላት ጠቀስም የአንዱ ወንጌላዊ አገላለጽ ከሌሎቹ የተለየ ስለሚሆን ሁሉንም የወንጌል ክፍል ማንበቡ አስፈላጊ ነው።
የዮሐንስ ወንጌል ነው። ይህም ወንጌል የመዘገበው እንደ ሦስቱ ወንጌላት ስለጌታ ታሪክና ሥራ ቢሆንም በብዛት እነርሱ ያልመዘገቡትን አንዳንድ ታሪክና ሥራዎች መዝግቦ ይገኛል። ስለዚህ በይዞታው ከሦስቱ ወንጌላት ይለያል። ሦስቱ ወንጌላትና አራተኛው ወንጌል በሚከተሉት ሦስት ነገሮች ይለያያሉ።
እነርሱም፦
✔ ሦስቱ ወንጌላት የጌታ የኢየሱስ ክርስቶስን ምድራዊውን ታሪክ (የትስብእቱን ማለት የሰውነቱን ነገር) አጉልተው ይጽፋሉ።
📗 ወንጌላዊው ማቴዎስ፦
አብርሃም ይስሐቅን ወለደ፡ ይስሐቅም ያዕቆብን ወለደ፡…ማታንም ያዕቆብን ወለደ፡ ያዕቆብም ክርስቶስ የተባለውን ኢየሱስን የወለደች የማርያምን እጮኛ ዮሴፍን ወለደ። ማቴ. ፩ ፡፩-፲፯ በማለት የጌታን የትውልድ ዝርዝር ጽፏል።
📒 ወንጌላዊው ማርቆስ፦
ኢየሱስና ደቀ መዛሙርቱም በፊልጶስ ቂሣርያ ወዳሉ መንደሮች ወጡ በመንገድም። ሰዎች እኔ ማን እንደ ሆንሁ ይላሉ? ብሎ ደቀ መዛሙርቱን ጠየቃቸው። እነርሱም። መጥምቁ ዮሐንስ፥ ሌሎችም ኤልያስ፥ ሌሎችም ከነቢያት አንዱ ብለው ነገሩት። እናንተስ እኔ ማን እንደ ሆንሁ ትላላችሁ? ብሎ ጠየቃቸው። ጴጥሮስም አንተ ክርስቶስ ነህ ብሎ መለሰለት። ማር.፰፡፳፯-፳፱ በማለት የጌታን የሰውነቱን ነገር ጽፏል።
📕 ወንጌላዊው ሉቃስ፦
ኢየሱስም ሊያስተምር ሲጀምር ዕድሜው ሠላሳ ዓመት ሆኖት ነበር፤ እንደመሰላቸው የዮሴፍ ልጅ ሆኖ የኤሊ ልጅ፡ የማቲ ልጅ፡…የሄኖስ ልጅ፡ የሴት ልጅ፡የአዳም ልጅ፡ የእግዚአብሔር ልጅ። ሉቃ.፫፡፳፫-፴፰። በማለት የጌታን የትውልድ ዝርዝር ጽፏል።
አራተኛው ወንጌል ግን ጌታ ከሰማይ መውረዱንና የመለኮቱን ነገር አጉልቶ ይጽፋል።
ይኸውም፦ በመጀመሪያው ቃል ነበረ፥ ቃልም በእግዚአብሔር ዘንድ ነበረ፥ ቃልም እግዚአብሔር ነበረ። ይህ በመጀመሪያው በእግዚአብሔር ዘንድ ነበረ። ሁሉ በእርሱ ሆነ፥ ከሆነውም አንዳች ስንኳ ያለ እርሱ አልሆነም። ዮሐ. ፩፡፩-፫ ከሰማይም ከወረደ በቀር ወደ ሰማይ የወጣ ማንም የለም፥ እርሱም በሰማይ የሚኖረው የሰው ልጅ ነው።
ዮሐ. ፫ ፡፲፫፤ እንግዲህ አይሁድ ከሰማይ የወረደ እንጀራ እኔ ነኝ ስላለ ስለ እርሱ አንጐራጐሩና አባቱንና እናቱን የምናውቃቸው ይህ የዮሴፍ ልጅ ኢየሱስ አይደለምን? እንግዲህ። ከሰማይ ወርጃለሁ እንዴት ይላል? አሉ። ኢየሱስ መለሰ አላቸውም። እርስ በርሳችሁ አታንጐራጕሩ። የላከኝ አብ ከሳበው በቀር ወደ እኔ ሊመጣ የሚችል የለም፥ እኔም በመጨረሻው ቀን አስነሣዋለሁ። ሁሉም ከእግዚአብሔር የተማሩ ይሆናሉ ተብሎ በነቢያት ተጽፎአል፤ እንግዲህ ከአብ የሰማ የተማረም ሁሉ ወደ እኔ ይመጣል።
አብን ያየ ማንም የለም፤ ከእግዚአብሔር ከሆነ በቀር፥ እርሱ አብን አይቶአል። እውነት እውነት እላችኋለሁ በእኔ የሚያምን የዘላለም ሕይወት አለው።
የሕይወት እንጀራ እኔ ነኝ። አባቶቻችሁ በምድረ በዳ መና በሉ ሞቱም፤ ሰው ከእርሱ በልቶ እንዳይሞት ከሰማይ አሁን የወረደ እንጀራ ይህ ነው። ከሰማይ የወረደ ሕያው እንጀራ እኔ ነኝ፤ ሰው ከዚህ እንጀራ ቢበላ ለዘላለም ይኖራል፤ እኔም ስለ ዓለም ሕይወት የምሰጠው እንጀራ ሥጋዬ ነው። ዮሐ. ፮፡፵፩-፶፩፤
እናንተ ከታች ናችሁ፥ እኔ ከላይ ነኝ፤ እናንተ ከዚህ ዓለም ናችሁ፥ እኔ ከዚህ ዓለም አይደለሁም። ዮሐ.፰፡፳፫ እንግዲህ ከላይ በተገለጹት የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍሎች ምክንያት ሦስቱ ወንጌላት ምድራውያን ወንጌላት ሲባሉ አራተኛው ወንጌል ደግሞ ሰማያዊ ወንጌል ይባላል።
.
.
.
#ይቀጥላል
@yetenantun_lenege
BY ማዕዶት ዘኦርቶዶክስ ተዋሕዶ
Warning: Undefined variable $i in /var/www/tg-me/post.php on line 280
Share with your friend now:
tg-me.com/yetenantun_lenege/345