Telegram Group Search
ከቅዱስ ሲኖዶስ የተሰጠ መግለጫ

በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን፡፡

ከኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን
ቅዱስ ሲኖዶስ የተሰጠ መግለጫ፡፡

በመንፈስ ቅዱስ የሚመራው የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ቅዱስ ሲኖዶስ በቅዱሳን አበው ሐዋርያት ትውፊት በፍትሕ መንፈሳዊ አንቀጽ 5 ቁጥር 164 በተደነገገው መሠረት ምልዓተ ጉባኤው የርክበ ካህናት መደበኛ ስብሰባውን ከግንቦት 21 እስከ ግንቦት 28 ቀን 2016 ዓ/ም ድረስ በርካታ አጀንዳዎችን በመቅረጽ ውይይት ሲያካሄድ ሰንብቷል፡፡

ምልዓተ ጉባኤው ለቤተ ክርስቲያናችን አንድነት፣ ለሐዋርያዊ ተልእኮ መስፋፋት፣ ለመንፈሳዊ ዕድገትና ለምእመናን ደኅንነት ትኩረት በመስጠት ለቅድስት ቤተ ክርስቲያናችንና ለሀገራችን ጠቃሚ የሆኑ ውሳኔዎችን አሳልፏል፡፡

በዚሁ መሠረት፡-

፩.በቅድስት ቤተ ክርስቲያንና በሀገራችን መንግሥት መካከል ሊኖር ስለሚገባው መልካም የሥራ ግንኙነት በቅዱስ ፓትርያርኩ መሪነት ከመንግሥት የሥራ ኃላፊዎች ጋር የሚመካከር የብፁዓን አበው ሊቃነ ጳጳሳት ልዑክ ቅዱስ ሲኖዶስ ሰይሟል፤

፪.በመላው ሀገራችን በተፈጠሩ ግጭቶች፣ አለመግባባቶችና የሰላም ዕጦት በርካታ የሰው ሕይወት መጥፋትና የንብረት ውድመት እንደቀጠለ መሆኑ ቅዱስ ሲኖዶስን በእጅጉ አሳዝኗል፡፡ ስለዚህ ጉዳዩ የሚመለከታቸው ሁሉም ባለድርሻ አካላት ከግጭትና ከጥፋት ድርጊት ተቆጥበው የተፈጠረውን አለመግባባትና ግጭት በውይይትና በምክክር እንዲፈቱ እና ዘላቂ ሰላም እንዲረጋገጥ ቅዱስ ሲኖዶስ በአጽንኦት ጥሪውን ያቀርባል፤

፫.በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር እየተከናወነ ባለው የኮሪደር ልማት ምክንያት ለፈረሱ የቤተ ክርስቲያናችን ይዞታዎች የከተማ አስተዳደሩ ምትክ ቦታ በመስጠትና ቤተ ክርስቲያናችን ወደ መልሶ ማልማት እንድትገባ ድጋፍ በማድረግ፤ በተለይም ክብርት ከንቲባ ወ/ሮ አዳነች አበቤ በፈረሰው የጽርሐ ምኒልክ የቤተ ክርስቲያኒቱ ሕንፃ ምትክ በከተማ አስተዳደሩ ሙሉ ወጭ ተጨማሪ ምድር ቤትና የቦታ ስፋት ያለው B+G+4 ሕንፃ ገንብቶ ለማስረከብ ቃል በመግባትና የቤተ ክርስቲያናችን የበላይ ኃላፊ አባቶች በተገኙበት የመሠረት ድንጋይ እንዲጣል ማድርጋቸውን ቅዱስ ሲኖዶስ ከምስጋና ጋር የተቀበለው ሲሆን በተሰጠን ምትክ ቦታ ላይም የከተማው ፕላን በሚፈቅደው መሠረት የመልሶ ማልማት ሥራው እንዲከናወን ቅዱስ ሲኖዶስ ወስኗል፡፡

፬.የሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን ከተቋቋመበት አዋጅ መረዳት እንደሚቻለው ባለድርሻ አካላትን ባሳተፈ ሁኔታ ሀገራዊ ችግሮችን በምክክርና በውይይት ለመፍታት የተቋቋመ መሆኑን ተረድተናል፡፡ ይሁን እንጅ ሀገረ መንግሥትን ከመመሥረት ጀምሮ በአስታራቂነትና በሰላም ግንባታ ግንባር ቀደም ተጠቃሽ ለሆነችው እናት ቤተ ክርስቲያን እስከአሁን ድረስ በይፋ የቀረበ የተሳትፎ ጥሪ ሳይኖር ኮሚሽኑ የተሳታፊ ልየታንና አጀንዳ መረጣ አጠናቆ ወደ ምክክር ትግበራ እየገባ መሆኑ ቅዱስ ሲኖዶስን ቅር አሰኝቷል፡፡ በመሆኑም የቤተ ክርስቲያኒቱ ተሳትፎና አጀንዳ የማቅረብ መብቷ እንዲረጋገጥ ከኮሚሽኑ ጋር በመነጋገር ጉዳዩን ተከታትሎ ለፍጻሜ የሚያበቃ ኮሚቴ ቅዱስ ሲኖዶስ ሰይሟል፡፡

፭.የብፁዓን አባቶች የዝውውርና የአህጉረ ስብከት ሥያሜን አስምልክቶ የቀረቡ ጥያቄዎችን ምልዐተ ጉበኤው ተመልክቶ ተገቢውን ውሳኔ አሳልፏል፤

፮.የሃይማኖት ጉዳዮች ረቂቅ አዋጅ ላይ ቅዱስ ሲኖዶስ በሰፊው ከተወያየ በኋላ በረቂቅ አዋጁ ሊሻሻሉ ይገባቸዋል ብሎ ያመነባቸውን የማሻሻያ ሐሳቦች በማዘጋጀት ለሚመለከተው መንግሥታዊ ተቋም እንዲላክና ረቂቅ አዋጁ ከመጽደቁ በፊት የተሰጡት የማሻሻያ ሐሳቦች በረቂቁ ስለመካተታቸው ክትትል የሚያደርግ ኮሚቴ ቅዱስ ሲኖዶስ ሰይሟል፡፡

፯.በቅዱሳት መጻሕፍት ላይ ተመሥርቶ አባታዊ ምክርና ተግሣጽ ማስተላለፍ ከቀድሞ ጀምሮ የነበረ መጽሐፍ ቅዱሳዊ መሠረት ያለው መሆኑ ቢታወቅም በሀገራችን ኢትዮጵያ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በተፈጠሩ አለመግባባቶች የተከሰቱትን ወቅታዊ ችግሮች አስመልክቶ እየተላለፉ ያሉ ቤተ ክርስቲያንን የማይወክሉ መልእክቶችን ቅዱስ ሲኖዶስ የማይቀበላቸውና በጥብቅ የሚቃወማቸው መሆኑን እየገለጸ ወደፊት እንዲህ ዓይነት ተመሳሳይ ድርጊት እንዳይፈጸም ለማድረግ ይቻል ዘንድ ወጥ የሆነ የመግለጫ አሰጣጥና የትምህርተ ወንጌል ተልእኮ ሕገ ደንብ ተዘጋጅቶ ለምልዐተ ጉበኤ እንዲቀርብ ቅዱስ ሲኖዶስ ወስኗል፤

፰.ግብረ ሰዶማዊነትና የተመሳሳይ ጾታ ጋብቻ በሕገ ተፈጥሮም ሆነ በሰው ልጅ የሰብዓዊ አኗኗር ፈጽሞ ተቀባይነት የሌለው፣ ፈጣሬ ዓለማት እግዚአብሔር መለኮታዊ ፈቃዱ በተገለጠባቸው ቅዱሳት መጻሕፍት ፈጽሞ የተከለከለ፣ በቀኖናተ ቤተ ክርስቲያን፣ በፍትሕ መንፈሳዊና በፍትሐ ብሔር ድንጋጌዎች፣ በሥነ ልቦና ደንቦች የተወገዘ፣ ሥነ አእምሮዊ ሚዛንን የሚያዛባ፣ ግለሰባዊ ማንነትን፣ ቤተሰባዊ ሕይወትን፣ ማኅበራዊ ትሥሥርን የሚጎዳ ተግባር በመሆኑ ቅዱስ ሲኖዶስ እያወገዘ የተመሳሳይ ጾታ ጋብቻና የግብረ ሰዶማዊነትን ኃጢአት በተመለከተ የቅድስት ቤተ ክርስቲያንን አቋም በሚገልጽ መልኩ ራሱን ችሎ ዓለም አቀፋዊ ይዘቱን ባገናዘበ ሁኔታ ዝርዝር መግለጫ እንዲሰጥ ቅዱስ ሲኖዶስ ወስኗል፤

፱.በደቡብ የሀገራችን ክፍል የቤተ ክርስቲያኒቱን አብነት ትምህርት ከማስፋፋትና ከፍ ያለ መዐርግ ከመስጠት አንፃር የጋሞና አካባቢው ዞኖች ሀገረ ስብከት የዝጊቲ ደብረ ሰላም አቡነ ገብረ መንፈስ ቅዱስ ቤተ ክርስቲያን የአራቱ ጉባኤያት ማስመስከሪያ ትምህርት ቤት እንዲሆን በቀረበው ጥናት መሠረት ቅዱስ ሲኖዶስ ለምሥክር ጉባኤ ቤቱ ዕውቅና በመስጠት ወደ ትግበራ እንዲገባ ወስኗል፡፡

፲.ከሀገራችን ውጭ ባሉ አህጉረ ሰብከት መደበኛ አገልግሎት ለመስጠት የሚላኩ አገልጋዮች በክፍሉ ሊቀጳጳስ ሲጠየቅ በሙያ ብቃታቸው፣ በምግባራቸውና በመንፈሳዊነታቸው የተመሰከረላቸው አገልጋዮች ከሁሉም አህጉረ ስብከት በብፁዓን ሊቃነ ጳጳሳት አቅራቢነት በውድድር እየተለዩ በቋሚ ሲኖዶስ ውሳኔ እንዲላኩ ቅዱስ ሲኖዶስ ወስኗል፡፡

፲፩.የቅድስት ቤተ ክርስቲያን አስተዳደር ዘመኑን የዋጀ እንዲሆን ቅዱስ ሲኖዶስ የዐሥር ዓመት መሪ ዕቅድ በማጽደቅ ወደ ትግበራ እንዲገባ መወሰኑ ይታወሳል፡፡ በዚሁም መሠረት ለአፈጻጸሙ ያመች ዘንድ በባለሙያዎች ተዘጋጅቶ የቀረበውን መዋቅራዊ አደረጃጀት በማጽደቅ በሕገ ቤተ ክርስቲያኑና በቃለ ዓዋዲው ተካቶ ሥራ ላይ እንዲውል ቅዱስ ሲኖዶስ ወስኗል፡፡

፲፪.በመንበረ ፓትርያርክ ጠቅላይ ቤተ ክህነት ጽ/ቤት ተዘጋጅቶ የቀረበውን የ2017 ዓ.ም. ዓመታዊ በጀት በማጽደቅ በሥራ ላይ እንዲውል ቅዱስ ሲኖዶስ ወስኗል፡፡

በአጠቃላይ ቅዱስ ሲኖዶስ በመንፈስ ቅዱስ እየተመራ ላለፉት ተከታታይ ቀናት በመንፈሳዊ፣ ማኅበራዊና ሀገራዊ ጉዳዮች ላይ በመወያየትና ተገቢውን ውሳኔ በማስተላለፍ መደበኛ ስብሰባውን በዛሬው ዕለት በጸሎት አጠናቅቋል፡፡ መሐሪና ሁሉን ቻይ የሆነ እግዚአብሔር አምላካችን ለሀገራችን፣ ለሕዝባችን፣ ለዓለሙ ሁሉ ሰላሙን፣ ፍቅሩንና አንድነቱን ይስጥልን፡፡

እግዚአብሔር ኢትዮጵያንና ሕዝቦቿን ይባርክ
ወስብሐት ለእግዚአብሔር አሜን

አባ ማትያስ ቀዳማዊ ፓትርያርክ
ርእሰ ሊቃነ ጳጳሳት ዘኢትዮጵያ
ሊቀ ጳጳስ ዘአክሱም
ወዕጨጌ ዘመንበረ ተክለ ሃይማኖት

ግንቦት ፳፱ ቀን ፳፻፲፮ ዓ.ም. ኢትዮጵያ አዲስ አበባ
©የቅዱስ ሲኖዶስ ጽ/ቤት
ከ6 ሚሊየን 50 ሺህ ዶላር የምዝበራ ሙከራ ጋር ተያይዞ የተከሰሱት እነ ቀሲስ በላይ ማረሚያ ቤት እንዲወርዱ ታዘዘ

ከአፍሪካ ሕብረት ሒሳብ 6 ሚሊየን 50 ሺህ ዶላር የምዝበራ ሙከራ ጋር ተያይዞ የተከሰሱት እነ ቀሲስ በላይ መኮንን ማረሚያ ቤት እንዲወርዱ ታዘዙ።

ተከሳሾቹ ማረሚያ ቤት ሆነው ጉዳያቸውን እንዲከታተሉ ትዕዛዙን የሰጠው የፌደራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ 3ኛ የሙስና ጉዳዮች ወንጀል ችሎት ነው።

ተከሳሾቹም÷ 1ኛ ቄስ በላይ መኮንን፣ 2ኛ በግብርና ኢንቨስትመንት ላይ የተሰማራው ኢያሱ እንዳለ ወ/መስቀል፣ 3ኛ በኮሚሽን ሥራ ላይ የተሰማራው በረከት ሙላቱ ጃፋር፣ 4ኛ አለምገና ሳሙኤል ዲንሳ እና 5ኛ የኒሞና ንግድ ሥራ ኃላ.የተ.የግል ማኅበር ሥራ አስኪያጅ አበራ መርጋ ተስፋዬ ናቸው።

ከ1ኛ እስከ 3ኛ ተራ ቁጥር የተጠቀሱት ችሎት የቀረቡ ሲሆን÷ 4ኛ እና 5ኛ ተከሳሾች ዛሬም ችሎት አልቀረቡም።

ችሎቱ ከዚህ በፊት በነበረ ቀጠሮ ተከሳሾች ክሱ እንዲሻሻልላቸው ያቀረቡት የመጀመሪያ ደረጃ የክስ መቃወሚያ ላይ ብይን ለመስጠት እና ዘግይተው የዋስትና ጥያቄ ባቀረቡት 3ኛ ተከሳሽ ዋስትና ላይ ብይን ለመስጠት በሰጠው ተለዋጭ ቀጠሮ መሰረት ተሰይሞ ብይን ሰጥቷል።

በዚህም ተከሳሾቹ ክሱ እንዲሻሻልላቸው ያቀረቡት የመጀመሪያ ደረጃ ክስ መቃወሚያ ነጥቦችን መርምሮ ወደፊት በማስረጃ እንደሚጣራ ገልጾ መቃወሚያቸውን አለመቀበሉን አብራርቷል።

ከሌሎች ተከሳሾች ተነጥለው ዘግይተው የዋስትና ጥያቄ ያቀረቡት 3ኛ ተከሳሽን በሚመለከት የተከሰሱበት ድንጋጌ ዋስትና በሚያስከለክል ከ10 ዓመት በላይ በሚያስቀጣ ድንጋጌ መከሰሳቸውን ጠቅሶ የዋስትና ጥያቄው ውድቅ ተደርጓል።

ተከሳሾቹ በክሱ ላይ የተጠቀሰውን የወንጀል ድርጊት መፈጸማቸውንና አለመፈጸማቸውን የማረጋገጫ ጥያቄ በፍርድ ቤት የተጠየቁ ሲሆን÷ ወንጀሉን አለመፈጸማቸውን ጠቅሰው የዕምነት ክህደት ቃላቸውን ሰጥተዋል።

ዐቃቤ ሕግ ምስክሮች እንዲሰሙለት ባቀረበው ጥያቄ መሰረት ፍርድ ቤቱ የምስክሮችን ቃል ለመስማት ለሰኔ 26 እና 27 ቀን 2016 ዓ.ም ተለዋጭ ቀጠሮ ሰጥቷል።

4ኛ እና 5ኛ ተከሳሾችን በሚመለከት ፖሊስ 4ኛ ተከሳሽ ይኖሩበታል የተባለው ቦታ የፀጥታ ችግር እንዳለ ጠቅሶ፤ 5ኛ ተከሳሽ ደግሞ በአድራሻቸው አለመገኘታቸውን ገልጾ ተጨማሪ ጊዜ እንዲሰጠው በጽሑፍ ጠይቋል።

የተከሳሽ ጠበቆችም በ4ኛ እና 5ኛ ተከሳሾች ምክንያት ጉዳያቸው እንዳይጓተትባቸው ስጋታቸውን ጠቅሰው አስተያየት ሰጥተዋል።

ፍርድ ቤቱም÷ ፖሊስ 4ኛ ተከሳሽ ያሉበት ቦታ የፀጥታ ችግር ስለመኖሩ ማረጋገጫ እንዲያቀርብ ያዘዘ ሲሆን፤ 5ኛ ተከሳሽን የወረዳው ነዋሪ መሆናቸው ወይም አለመሆናቸውን ከወረዳው ማረጋጋጫ እንዲያቀርብ ትዕዛዝ ሰጥቷል፡፡

በታሪክ አዱኛ
የማጽናኛ ጉባኤ ተዘጋጅቷልና ሁላችሁም ቤተሰቦቻችን በፈረንሳይ አቡነ ገብረ መንፈስ ቀዱስ ቤተክርስቲያን (ቀበና አቦ) ሰኔ 05- ዕለተ ረቡዕ በዛ ተገናኝተን በጸሎት በምስጋና ወንድማችንን ስናስበው እናመሻለን
#ሙሉ_ቃል

ቅዱስ ሲኖዶስ ስለ ብፁዕ አቡነ ሉቃስ ምን አለ ?

" ' ግደሉ ብሎ ' ማወጅ ቤተክርስቲያኒቱን የማይወክል እና ቅዱስ ሲኖዶስን የማይመጥን ንግግር ነው " - ቅዱስ ሲኖዶስ

ቅዱስ ሲኖዶስ ያሳለፈውን ውሳኔ ያቀረቡት ብፁዕ አቡነ አብርሃም ናቸው።

ብፁዕ አቡነ አብርሃም በንባብ ያሰሙት ፦

" በአሁኑ ሰዓት ላይ ትልቅ ተግዳሮትና የፈተና ምንጭ በመሆን ቤተክርስቲያናችንን ዋጋ እያስከፈሏት ያሉትን የአንዳንድ አባቶች መግለጫ እና የአውደ ምህረት ትምህርቶች እንደ አብነት በመጥቀስ የቅዱስ ሲኖዶስ ምልዓተ ጉባኤ በሰፊው ተወያይቷል።

በውይይቱ የተለዩ ዋና ዋና ነጥቦች ፦

- አብዛኛው የአውደ ምህረት ስብከቶቻችን ከትምህርተ ወንጌል ይልቅ የነገር እና የደረቅ ትችት መድረክ እየሆኑ መምጣታቸው ፤

- በተለይም በመዋቅር ውስጥ የስራ መደብ የሌላቸው ተዘዋዋሪ " #ሰባኪ_ነን_ባዮች " የወገንተኝነት እና የፖለቲካ ትችትን እንደ ተከታይ ማፍሪያ በመቁጠር በሚዘሩት ፍጹም ከቃለ ወንጌል የራቀ ዘር ቅድስት ቤተክርስቲያንን ዋጋ እያስከፈላት መሆኑ ፤ ይህን ለመከላከል ጥረት በሚያደርጉ አህጉረ ስብከት ላይ ትልቅ የመልካም አስተዳደር ችግር እየተፈጠረ መሆኑ ፤

- በተለይም ብጹዕ አቡነ ሉቃስ የምስራቅ አውስትራሊያ እና በመንበረ ፓትርያርክ ጠቅላይ ቤተክህነት ፅ/ቤት የገዳማት አስተዳደር መምሪያ የበላይ ኃላፊ ሊቀጳጳስ ታህሳስ 19 / 2016 ዓ/ም በሀገረ አሜሪካ በዋሽንግተን ዲሲ እና አካባቢው ሀገረ ስብከት በሜሪላንድ ከተማ ሐመረብርሃን ቅዱስ ዮሐንስ ወቅዱስ ገብርኤል ቤተክርስቲያን በዓለ ንግስ ላይ ታቦተ ህጉ በቆመበትና ምእመናንም በተሰበሰቡበት እንደ ቀኖና ቤተክርስቲያን ዕለቱን አስመልክቶ ተገቢውን ትምህርተ ወንጌል ከመስጠት ይልቅ ቤተክርስቲያንን የማይመጥን እና የቅዱስ ሲኖዶስን ልዕልና ብሎም የአባትነትን ክብር ዝቅ በሚያደርግ ሁኔታ አንድን የተከበረ ጠቅላይ ሚኒስትር ፦

° " #ግድሉ "
° " #ዘርህ_ይጥፋ "
° " #የአድማ_ብተና_ይበትንህ " የሚሉ ህገወጥ እና ክብረነክ የሆኑ ንግግሮች በመናገር በፈጸሙት ያልተገባ ተግባር በቤተክርስቲያኒቱ እና በመንግስት መካከል የነበረውን ግንኙነት በማሻከር ቤተክርስቲያንን ብዙ ዋጋ እያስከፈላት ከመሆኑ በላይ ለዘመናት ጸንቶ የቆየውን የአባቶችን ክብር እና የቅዱስ ሲኖዶስን ልዕልና ዝቅ ያደረገ ተገቢነት የሌለው አድርጎት መሆኑን፤

- ክብር ይግባውና ጌታችን፣ አምላካችን መድሃኒታችን ኢያሱስ ክርስቶስ በማትዮስ ወንጌል ምዕራፍ አምስት ቁጥር ሰላሳዘጠኝ ላይ እንደተናገረው " እኔ ግን እላችኋለሁ ጉንጭህን በጥፊ ለሚመታህ ሁሉ ሁለተኛውን ደግመህ አዙርለት " ብሎ ያስተማረውን አብነት አድርጋ አትግደል የሚለውን ህገ ኦሪት አጽንታ እያስተማረች እስካሁን ድረስ ጸንታ በቆየችው እናት ኦርቶዶክሳዊት ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን አውደምህረት ላይ " ግደሉ " ብሎ ማወጅ ቤተክርስቲያኒቱን የማይወክልና ቅዱስ ሲኖዱስን የማይመጥን ንግግር መሆኑን ፤

- ልክ እንደ አቡነ ሉቃስ ፈጽሞ ጫፍ የረገጠ ባይሆንም ሌሎችም #አንዳንድ_አባቶች በተለያዩ ቦታዎች ያስተላለፏቸው መልዕክቶች አግባብነት የሌላቸውና ቤተክርስቲያንን ለትችት የዳረጉ መሆናቸውን ምልዓተ ጉባኤው በዝርዝር ገምግሟል።

ውሳኔ ፦

1ኛ. ብጹዕ አቡነ ሉቃስ የምስራቅ አውስትራሊያ እና በመንበረ ፓትርያርክ ጠቅላይ ቤተክህነት ፅህፈት ቤት የገዳማት አስተዳደር መምሪያ የበላይ ኃላፊ ሊቀጳጳስ ታህሳስ 19 ቀን 2016 ዓ/ም በሀገረ አሜሪካ በዋሽንግተን ዲሲ እና አካባቢው ሀገረ ስብከት በሜሪላንድ ከተማ ሐመረብርሃን ቅዱስ ዮሐንስ ወ ቅዱስ ገብርኤል ቤተክርስቲያን አውደምህረት ላይ " ግደሉ ፣ ዘርህ ይጥፋ፣ የአድማ ብተና ይበትንህ " ... ሌሎች ከቀኖና ቤተክርስቲያን ውጭ የሆኑ ንግግሮች ቤተክርስቲያኒቱንም ሆነ ቅዱስ ሲኖዶስን የማይወክል ከቤተክርስቲያኒቱ አስተምህሮ እና ቀኖና ውጭ የሆነ ከህገ ኦሪትም ሆነ ከቃለ ወንጌል ያፈነገጠ ንግግር መሆኑ ፤

2ኛ. በቀጣይም እንዲህ አይነት ተመሳሳይ ስህተት #በብዑጽነታቸው ሆነ በአንዳንድ አባቶች ሰባክያን ወንጌል እንዳይደገም ተፈጽሞም ቢገኝ ተገቢው የእርምት ውሳኔ ለመስጠት ይቻል ዘንድ የመግለጫ አሰጣጥ እና የትምህርተ ወንጌል አሰጣጥ አስመልክቶ ገዢ የሆነ ህገ ደንብ በመንበረ ፓትርያርክ ጠቅላይ ቤተክህነት አገልግሎት መምሪያ እና በሊቃውንት ጉባኤ በኩል ተዘጋጅቶ ለጥቅምት 2017 ዓ/ም ምልዓተ ጉባኤ እንዲቀርብ ፤

3ኛ. ይህ ውሳኔ ከተወሰነበት ዕለት ጀምሮ በመላው ዓለም የሚገኙ አህጉረ ስብከት ተመሳሳይ ስህተት እንዳይፈጸም ተገቢውን ቁጥጥር እና ክትትል እንዲያደርጉ ፤ ከክትትል እና ከቁጥጥር ጉድለት ምክንያት በየትኛውም የቤተክርስቲያኒቱ አውደምህረት ላይ ለሚተላለፉ የተሳሳቱና ከቀኖና ቤተክርስቲያን ያፈነገጡ ትምህርቶች እና ንግግሮች በኃላፊነት የሚያስጠይቅ መሆኑን ለሁሉም ሀገረ ስብከት በመንበረ ፓትርያርክ ጠቅላይ ቤተክህነት በኩል ጥብቅ መመሪያ እንዲተላለፍ በማለት ቅዱስ ሲኖዶስ ወስኗል።

ይህ ሙሉ ቃል የቅዱስ ሲኖዶስ ውሳኔ ነው። "
ዋስትና ብይን ለመስጠት ለአራተኛ ግዜ ዛሬ ከሰዓት ልደታ ከፍተኛ ፍ/ቤት ይቀርባሉ
እመብርሀን ከጎንህ ትሁን ሌላ ምን ይባላል
መርጌታ ብርሃኑ ተ/ያሬድን ጨምሮ ከ 80 ሰው በላይ ዛሬ ከሰዓት ልደታ ከፍተኛ ፍ/ቤት ለዋስትና ብይን የቀረቡ ሲሆን ፤ በዋስ ይለቀቁ የሚለው የጠበቆቹን ጥያቄ ዳኞቹ ውድቅ በማድረግ መርማሪ የጠየቀው 14 ቀን ፈቅደው ለሰኔ 12 ተቀጥረዋል።
ይሄን እወቁ
አቡነ ሩፋኤል 7 ሐገረ ስብከት ተሰጣቸው ምክንያቱም በጥቅምት ወር 9 ጳጳሳት ካልተሾሙ ተብሎ አስገድደው በኦሮምያ ያንሳል ብለው ተሾሙ ለ ኦሮሞ ብቻ 9 ጳጳስ ይሁን አልን ተቀበልን አመት ሳይሞላቸው በስረአት አገልግሎት ሳይሰጡ ቦታ ቀይሩኝ አልተመቸንም አሉ ቆይ ምላተ ጉባኤው ቅዱሱ ሲኖዶስ ምን ነክቶት ነው ይሄን መርምሮ ይሆን ለ አቡነ ሩፋኤል 7 ሐገረ ስብከት የሰጡት በምን ሁኔታ ታይቶ ነው ጳጳስ ያንሳል አሉ ተሾመላቸው ለገንዘብ ስለተሾሙ እንዴት ስራ ይስሩ ቅዱስ ሲኖዶስ ለምን መፈተሽ ተሳነው እንዴትስ ለአንድ ጳጳስ ይሄ ሁሉ ሐገረ ስብከት ይሰጠዋል ሌሎቹስ ስራቸው ምንድነው ለነገሩ 4ኪሎ መኖር ከጀመሩ ወዲህ ነው ቤተ ክርስትያን እየተደፈረች የመጣቺው ሁሉም ሐገረ ስብከቱላይ ሆኖ ነፍስ ቢያድን የት በደረስን ግን መፍትሄው ከክርስቶስ ውጪ ምንም ተስፋ የለንም እኔ በጣም አስገርሞኛል ያሁኑ ውሳኔ ምንም የተለየ ነገር አላየሁትም አስከፍቶኛል ግን በተስፋ እጠብቃለሁ።
+ ረቢ ወዴት ትኖራለህ? +

ከመጥምቁ ዮሐንስ ተማሪዎች መካከል ሁለቱ "የእግዚአብሔር በግ እነሆ" የሚለውን የመምህራቸውን ስብከት ሰምተው ጌታን ተከተሉት::

"ኢየሱስም ዘወር ብሎ ሲከተሉትም አይቶ፦ ምን ትፈልጋላችሁ? አላቸው። እነርሱም፦ ረቢ፥ ወዴት ትኖራለህ? አሉት፤ መጥታችሁ እዩ፡ አላቸው። መጥተው የሚኖርበትን አዩ፥ በዚያም ቀን በእርሱ ዘንድ ዋሉ፤ አሥር ሰዓት ያህል ነበረ" ዮሐ. 1:37-39

ጌታን ተከትለው የሚኖርበትን ካዩት ደቀ መዛሙርት አንደኛው ስም እንድርያስ ሲሆን ሁለተኛው ደግሞ የራሱን ስም በወንጌሉ ላይ እኔ የማይጽፈውና ቤተ ክርስቲያን ግን የራሱን ነገር ሲገልፅ በሚጠቀመው ቋንቋ የምታውቀው ወንጌላዊው ዮሐንስ ነበረ::

"ረቢ፥ ወዴት ትኖራለህ? አሉት፤ መጥታችሁ እዩ፡ አላቸው። መጥተው የሚኖርበትን አዩ" የሚለው ቃል በእርግጥ በጣም አስገራሚ ነው:: የክርስቶስን መኖሪያ ማየት መፈለጋቸው ፈልገው እንዳያጡት አድራሻውን ለማወቅ ካላቸው ጉጉት የተነሣ ነበረ::
ሆኖም ክርስቶስ በምድር ላይ ሲኖር ቋሚ አድራሻ አልነበረውም:: ራሱ እንደተናገረ :-ለቀበሮዎች ጉድጓድ ለሰማይም ወፎች መሳፈሪያ አላቸው፥ ለሰው ልጅ ግን ራሱን የሚያስጠጋበት የለውም" (ማቴ. 8:20)

እነዚህ ሁለት ደቀ መዛሙርት የጠየቁት "ረቢ፥ ወዴት ትኖራለህ?" የሚለው ጥያቄ አድራሻ ከመጠየቅ ከፍ ያለ ጥልቅ ጥያቄ ነው:: ነቢያቱ "የጥበብ ሀገርዋ ወዴት ነው? ማደሪያዋስ ወዴት ነው?" ብለው የተጨነቁለት የጥበብ ክርስቶስ ማደሪያ የት እንደሆነ ማወቅ የነፍስ ዕረፍት ነውና ተራ ጥያቄ አይደለም?
ይህ ጥያቄ ዳዊት ለዓይኖቹ እንቅልፍ ለሽፋሽፍቶቹ ዕረፍት ያልሠጠበት "የያዕቆብ አምላክን ማደሪያ እስኪያገኝ ድረስ" የለመነበት ጥያቄ ነው::

ረቢ ወዴት ትኖራለህ? የሚለው ጥያቄ እንድርያስና ዮሐንስ በአንድ ቀን ብቻ የሚመለስ ጥያቄ መስሎአቸው አብረውት ሔደው አብረውት ዋሉ እንጂ የጌታ መኖሪያ ግን ያን ቀን የዋለበት ብቻ አይደለም::

ረቢ ወዴት ትኖራለህ?
"ብርሃንህንና እውነትህን ላክ፤ እነርሱ ይምሩኝ፥ ወደ ቅድስናህ ተራራና ወደ ማደሪያህ ይውሰዱኝ" መዝ. 43:3

ረቢ ወዴት ትኖራለህ?  "ወደ ሰማይ ብወጣ፥ አንተ በዚያ ነህ፤ ወደ ሲኦልም ብወርድ፥ በዚያ አለህ። እንደ ንስር የንጋትን ክንፍ ብወስድ፥ እስከ ባሕር መጨረሻም ብበርር፥  በዚያ እጅህ ትመራኛለች፥ ቀኝህም ትይዘኛለች" መዝ. 139:8 ለአድራሻ የሚያስቸግረው የረቢ መኖሪያው ብዙ ስለሆነ የት ትኖራለህ ለሚለው ጥያቄ መልሱ "መጥታችሁ እዩ" ብቻ ነው::

ረቢ ወዴት ትኖራለህ? ብለው ለጠየቁት ደቀ መዛሙርቱ ቦታውን ከመናገር ይልቅ  "መጥታችሁ እዩ" ያለው ጌታ እርሱን ጸንተው እስከተከተሉ ድረስ በሕይወታቸው ዘመን ሁሉ አልፎም ከሞቱ በኋላ የሚያዩት ብዙ መኖሪያ ስላለው ነበር::

የረቢ መኖሪያው ብዙ ነው:: "የሚወደኝ ቢኖር ቃሌን ይጠብቃል፤ አባቴም ይወደዋል፡ ወደ እርሱም እንመጣለን፡ በእርሱም ዘንድ መኖሪያ እናደርጋለን" እንዳለ ቃሉን የሚጠብቅ ሰው ሰውነትም የእርሱ ማደሪያ ነው:: (ዮሐ. 14:23)

ረቢ ወዴት ትኖራለህ? " በአባቴ ቤት ብዙ መኖሪያ አለ፤ እንዲህስ ባይሆን ባልኋችሁ ነበር፤ ስፍራ አዘጋጅላችሁ ዘንድ እሄዳለሁና" ስትል ሰምተንህ ነበር:: (ዮሐ. 14:2) የአንተ መኖሪያ መንግሥተ ሰማያት አይደለምን?  ቅዱስ ጳውሎስ "ልሔድ ከክርስቶስ ጋር ልኖር እናፍቃለሁ" ሲል እንደሰማነው እስከ ዐሥር ሰዓት ድረስ እንደመዋል ዐሥሩ መዓርጋት ላይ የደረሱ በጽድቅ መንገድ የሔዱ የሚያዩት ማደሪያህ መንግሥተ ሰማያት አይደለምን? መጥተን ለማየት "እናንተ የአባቴ ቡሩካን ወደ እኔ ኑ" እስክትለን በተስፋ እየጠበቅን አይደለምን?

ረቢ ወዴት ትኖራለህ? ካሉት ጠያቂዎች መካከል አንዱ ዮሐንስ መሆኑን ሳስብ ደግሞ ዮሐንስ ያያቸው የረቢ መኖሪያዎች ከገሊላ እስከ ታቦር ተራራ ፣ ከሊቶስጥራ እስከ ቀራንዮ ፣ ከወንጌል እስከ ራእይ እጅግ ብዙ እንደነበሩ ታየኝ::

"ወዴት ትኖራለህ?" ብሎ ጠይቆ ጌታን የተከተለው ዮሐንስ "መጥተህ እይ" በተባለው መሠረት የጌታን መኖሪያ የእርሱን ያህል ያየም ሰው የለም::

ዮሐንስ "ረቢ ወዴት ትኖራለህ?" ለሚል ጥያቄው ግን አንጀት የሚያርስ ልብ የሚያሳርፍ መልስ ያገኘው አርብ ዕለት መስቀሉ ሥር ነበር:: ወዴት ትኖራለህ? ላለው ዮሐንስ የዘጠኝ ወር ከተማውን የዘላለም ማረፊያውን "እነኋት እናትህ" ብሎ ሲሠጠው መጥቶ ካያቸው የረቢ መኖሪያዎች ሁሉ የምትበልጠውን መኖሪያ አየ:: "እግዚአብሔር ጽዮንን መርጦአታልና፥ ማደሪያውም ትሆነው ዘንድ ወድዶአታልና፥ እንዲህ ብሎ፦  ይህች ለዘላለም ማረፊያዬ ናት፤ መርጫታለሁና በዚህች አድራለሁ" ብሎ የመረጣትን ማደሪያ ከማየት በላይ ምን ክብር አለ? (መዝ. 132:13)

ዮሐንስ ይህችን የረቢ መኖሪያ ወዲያው ወደ ቤቱ ወሰዳት:: ዮሴፍ ሊወስዳት ስላልፈራ ምን እንዳገኘ ያውቃልና እርሱም ይህችን የዕንቁ ሳጥን ወደ ቤቱ ወስዶ ቢዝቁት የማያልቅ ጸጋን ተጎናጸፈ::

ጌታ እናቱን ለዮሐንስ መሥጠቱ የሁለት ድንግልናዎች ማስረጃ ሆነ:: የድንግል ማርያም ዘላለማዊ ድንግልናም የዮሐንስ ድንግልናም በጌታ ንግግር ታወቀ:: 

አንዳንዶች እንደሚመስላቸው ድንግል ማርያም ከጌታ ሌላ ልጆች ቢኖሩአት ኖሮ "እናቴን ከልጆችዋ ነጥለህ ወደ ቤትህ ውሰዳት" "አንቺም ልጆችሽን ይዘሽ ወደ ሰው ቤት ሒጂ" ብሎ ለዮሐንስ አይሠጣትም ነበር:: ድንግል ማርያም የአብን አንድያ ልጅ አንድያ ልጅዋ አድርጋለችና አምላክ ባደረበት ዙፋን ሌላ ፍጡር ያላስቀመጠች የአምላክ ብቸኛ ዙፋን ፣ እግዚአብሔርን አስገብታ በርዋን የዘጋች ዘላለማዊት ድንግል መሆንዋ ለዮሐንስ በመሠጠትዋ ታወቀ:: ዮሐንስም ቤት ንብረት የሌለው መናኝ ባይሆንና ሚስት ድስት ያለው ሰው ቢሆን ድንገት ወደ ቤቱ ይዞአት እንዲሔድ እናቱን ባልሠጠው ነበር::

የሰው ልጅ ድኅነት ታሪክ በሁለት "እነሆ"ዎች መሃል መከናወኑ እጅግ ይደንቃል:: የሰው መዳን የተጀመረው "እነሆኝ የጌታ ባሪያ" ብላ ራስዋን ለፈጣሪ በሠጠችው ድንግል ቃል ሲሆን የተጠናቀቀው ደግሞ "እነኋት እናትህ" ብሎ በደም በታጠበ አንደበቱ በነገረን የኑዛዜ ቃል ነው::

ረቢ ወዴት ትኖራለህ? ለእኛም አታሳየን ይሆን? እስከ ዐሥር ሰዓት መዋል ፣ ዐሠርቱን ትእዛዛትህን ፣ ዐሥሩን የቅድስና ደረጃዎችን መውጣት ላቃተን ለእኛስ መኖሪያህን ታሳየን ይሆን? መጥታችሁ እዩ የሚለውን ጥሪ ሰምተን ለማምጣት አቅም ላነሰን መጻጉዕዎች ፣ ዓይን ላጣን በርጤሜዎሶች ተነሡ እዩ ብለህ መኖሪያህን አታሳየን ይሆን? መቅደስህን እንመለከት ዘንድ ፣ መኖሪያህን መንግሥትህን እናያት ዘንድ ፣ ዮሐንስ ያያትን መኖሪያህ እናትህን እናይ ዘንድ እንመኛለን::

ረቢ ወዴት ትኖራለህ?

ዲያቆን ሄኖክ ኃይሌ
መስከረም 21 2016 ዓ.ም. ተጻፈ

"ማርያም ገጸኪ እፈቱ ርእየ
ድንግል ድንግል ንዒ ኀቤየ
እስመ ኪያኪ ጸምአት ነፍስየ"
ወተዘከርኒ ለኃጥእ ገብርኪ ተክለ ማርያም
ጻድቁ አባ ጉባ

በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን !!!

ለጻድቁ አባታችን ወርሃዊ የመታሰቢያ በዓል ያደረሰን አምላክ የተመሰገነ ይሁን !!!

⛪️ ታህሣሥ ፳፱ ቀን በ፫፻፴፮ /336/ ዓ.ም ተወለዱ። አባታቸው ጌርሎስ እናታቸው ደግሞ ቴዎዶክስያ ይባላሉ። በእግዚአብሔር ፊት መልካም የሚያደርጉ ነበሩ።

⛪️ ጉባ የሚለው የስማቸው ትርጉሙ "አፈ መዐር፣ ጥዑመ ልሳን" ማለት ነው።
ከዘጠኙ ቅዱሳን አንዱ የሆኑት አባ ጉባ የትውልድ ሀገራቸው ኪልቂያ ይባላል።

⛪️ በልጅነታቸው መጽሐፍትን አጥንተው ወደ ገዳመ አሰቄጥስ ገብተው የመነኑት አባ ጉባ በአራተኛው መቶ ክፍለ ዘመን አጋማሽ ከስምንቱ ቅዱሳን ጋር በቅዱስ ገብርኤል መሪነት ወደ ኢትዮጵያ ገቡ።

⛪️ ጻድቁ አባ ጉባ እንደ ሌሎቹ ቅዱስን ሁሉ በስብከተ ወንጌል፣ መጻሕፍትን በመተርጎም፣ ገዳማትን በማስፋፋትና አብያተ ክርስቲያናትን በማነጽ ላይ በስፋት ሲንቀሳቀሱ ቆይተዋል። በዚህም አገልግሎታቸው የክርስትና ሃይማኖት ኢትዮጲያ ውስጥ እንዲስፋፋ ያደረጉ ታላቅ አባት ናቸው። እርሳቸው ከመሰረቷቸው ገዳማቶች ውስጥ አንዷ በሰሜን ወሎ የምትገኘው ራማ ኪዳነ ምህረት ናት።

⛪️ ጻድቁ ቅዳሴ ሲገድሱ ከመሬት ከፍ ከፍ ይሉ ነበር። በጸሎታቸው ብዙዎች ድነዋል፣ ጸበሎች ፈልቀው ድውያን ተፈውሰዋል።

⛪️ ጻድቁ ከበርካታ የቅድስና አመታት አገልግሎት በኋላ በግንቦት ፳፱ /29/ ቀን ከዚህ ዓለም ድካም አረፉ፤ በገዳማቸውም ተቀበሩ። ወር በገባም በቀን ፪ ይታሰባሉ።

የጻድቁ አባት አባ ጉማ ምልጃ አይለየን፤ በረከታቸውም ይደርብን።
በዓታ ለማርያም

ለወርሃዊው እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ወደ ቤተ መቅደስ ለገባችበት ቀን (በዓታ ለማርያም) ያደረሰን አምላክ ይመስገን !!!

" ልጄ ሆይ፥ ስሚ እዪ ጆሮሽንም አዘንብዪ፤ ወገንሽን ያባትሽንም ቤት እርሺ፤ ንጉሥ ውበትሽን ወድዶአልና፥ እርሱ ጌታሽ ነውና።"
መዝ. ፵፭፥፲-፲፩ /45፥10-11/

⛪️ ንጽሕተ ንጹሐን፣ ቅድስተ ቅዱሳን፣ ከተመረጡ የተመረጠች፣ ከተለዩ የተለየች፣ ከተከበሩ የተከበረች እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ከወላጆቿ ተለይታ በዚህች ቀን ወደ ቤተ መቅደስ ገባች።

⛪️ ቤተሰቦቿ እስከ ሶስት ዓመትዋም በንጽሕና ሲያሳድጓት ቆዩ። የስዕለታቸውን ነገር አንስታ ቅድስት ሐና "ልጃችን ቤተ እግዚአብሄርን ልታገለግል እንጂ በዚህ ዓለም እኛን ልታገለግል እንዳልተሳልን አስብ" ብላ ለቅዱስ ኢያቄም ነገረችው። እርሱም በሰማው ነገር ተደሰተ።

⛪️ እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ወደ እግዚአብሔር ቤተ መቅደስም በገባች ጊዜ እድሜዋ ሶስት ዓመት ነበር።

⛪️ ለ፲፪ ዓመታትም ሰማያዊ ኅብስትና መጠጥ እየተመገበች በቤተ መቅደስ ኖረች። በንጽሕናና በመልካም አካሄድ በእግዚአብሔር ፊት ተመላለሰች።

⛪️ ይህም ወደ ቤተ መቅደስ የገባችበት ቀን በኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን ወር በገባ በቀን ሶስት እየታሰበ ይከበራል።

የእናታችን በረከት ከሁላችንም ጋር ይሁን። ምልጃና ጸሎቷ አይለየን።
ሊቀ መላእክት ቅዱስ ፋኑኤል

አንድ አምላክ በሚሆን በአብ በወልድ በመንፈስ ቅዱስ ስም አሜን!

እንኳን ለሊቀ መላእክት ቅዱስ ፋኑኤል ወርሃዊ የመታሰቢያ በዓል አደረሳችሁ፣ አደረሰን !!!

⛪️ ቅዱስ ፋኑኤል ከሰባቱ ሊቃነ መላእክት አንዱ ነው። ሰዳዲ ሰይጣናት ወመድፍ አጋንንት እየተባለ ይጠራል።ይህም ትርጉሙ "ሰዎችን በልዩ ልዩ በሽታዎች እና እንቅፋቶች የሚያሰናክሉ አጋንንትን እያሳደደ ወደ ጥልቁ የሚከታቸው መልአክ" ማለት ነው።

⛪️ እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ወደ እግዚአብሔር ቤተ መቅደስ በ፫ ዓመቷ በገባች ቀን ሰማያዊ ጽዋንና ሰማያዊ ኅብስትን ይዞ መጥቶ የመገባት መልአክ ቅዱስ ፋኑኤል ነው።

⛪️ በ፪ኛ ነገስት ላይ እንደተጠቀሰው የሶሪያ ንጉሥ እስራኤልን በቁጥጥር ስር ባደረገ ጊዜ ኤልሳንና የእስራኤልን ልጆች ለማዳን ቅዱስ ፋኑኤል ሰራዊቱን አስከትሎ በከተማዋ ሰፈረ፤ የጠላትን አይን አሳውሮ ኤልሳና እስራኤላውያን ከጠላት ታድጓል። ( ፪ኛ ነገ. ፮፥፲፬)

⛪️ የሊቀ መላእክት ቅዱስ ፋኑኤል መታሰቢያ ወር በገባ በቀን ፫ የሚከበር ሲሆን የንግረዠሥ በዓሉ ደግሞ ታህሣሥ ፫ ቀን በድምቀት ይከበራል።

ዛሬም ጥበቃውን የማያቋርጠው ቅዱስ መልአክ በዙሪያችን ይገኝ ዘንድ፣ ጥበቃና ጸሎቱ ከእኛ ጋር ይሁን። አሜን።
እጅግ የምወደው ወንድሜ ጓደኛዬ ወጃጄ የሆነው ዘማሪ ዲን ዮሐንስ ዘመርቆርዬስ አላውቀውም ብዬ በሚል የዝማሬ ርዕስ በአዲስ መዝሙር ብቅ ብሏል በቅርብ ቀን ይጠብቁን።
በአቃቂ መንበረ ሕይወት መድኃኔዓለም ደብር ሰኔ 6 ለሚከበረው የጌታችን እና መድሃኒታችን እየሱስ ክርስቶስ የዕርገት ክብረ በአል የተደረጉ ቅድመ ዝግጅቶች
2024/06/11 13:48:50
Back to Top
HTML Embed Code: