Telegram Group Search
መልእክተ ቅዱስ ፓትርያርክ

በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን!
- ብፁዕ አቡነ አብርሃም
የጠቅላይ ቤተ ክህነት ዋና ሥራ አስኪያጅ
የሰሜን ጎጃምና የባሕር ዳር አህጉረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ
- ብፁዓን አበው ሊቃነ ጳጳሳት የቅዱስ ሲኖዶስ አባላት!
እግዚአብሔር አምላካችን በቤተ ክርስቲያን ላይ በየጊዜው የሚደርሰውን ፈተና በማስቻል ለዚህ ሲኖዶሳዊ ምልአተ ጉባኤ እንኳን በሰላም አደረሰን!

‹‹አስተብቊዓክሙ አኃዊነ በስሙ ለእግዚእነ ኢየሱስ ክርስቶስ ከመ ትበሉ ኵልክሙ አሐደ ቃለ ወአሐደ ነገረ ወትኩኑ ፍጹማነ ወኢትትፋለጡ ወሀልዉ በአሐዱ ምክር ወበአሐዱ ልብ፤ ወንድሞች ሆይ ሁላችሁ አንድ ንግግር እንድትናገሩ፣ በአንድ ልብና በአንድ ሐሳብም የተባበራችሁ እንድትሆኑ እንጂ መለያየት በመካከላችሁ እንዳይሆን በጌታችን በኢየሱስ ክርስቶስ ስም እለምናችኋለሁ›› (፩ቆሮ ፩፥፲)፡፡

ቅዱስ ጳውሎስ ይህንን መልእክት ለቆሮንቶስ ሰዎች ለመጻፍ ሲያስብ አንድ ዓቢይ ምክንያት እንዳለው ከመልእክቱ ይዘት መረዳት ይቻላል፤ የቆሮንቶስ ክርስቲያኖች አንድነትንና ሰላምን ፍቅርንና መተባበርን ከምትሰብከው ወንጌለ መንግሥተ እግዚአብሔር ወጥተው ብዙ ርቀት ሂደዋል፤ አንድነቱ፣ ኅብረቱ መረዳዳቱ መተጋገዙና መተባበሩ ከመካከላቸው ጠፍቶአል፤ ሌላው ቀርቶ ቅዱስ ቊርባንን ለመቀበል በሚሰበሰቡበት ጊዜ እንኳ የሀብታምና የድሀ የሚል ክፍፍል ተፈጥሮ ቤተ ክርስቲያኗን አደጋ ላይ ጥሎአል፡፡
ቅዱስ ጳውሎስ ይህንን እና ይህንን የመሳሰለ ፈተና በቆሮንቶስ ቤተ ክርስቲያን ሥር እየሰደደ መምጣቱን በእጅጉ አሳስቦታል፤ ይህ የሰላምና የአንድነት ጠንቅ የሆነው የመለያየት አዝማሚያ በጣም ሰፍቶ ቤተ ክርስቲያንን ከማፍረሱ በፊት በትምህርት በምክርና በተግሣጽ ማረም እንዳለበት ቅዱስ ጳውሎስ ተገንዝቦአል፤ እሱ ራሱም በአካል በመካከላቸው ተገኝቶ ሊያስተካክላቸው ፈቃደኛ ነበረ፤ ነገር ግን እሱ በዚህ ጊዜ በሮም ውስጥ እስር ቤት ላይ ስለነበረ አልቻለም፤ የነበረው አማራጭ በጽሑፍ ማስተማርና መምከር ነውና፤ ይህንን መልእክት ጽፎላቸዋል፡፡

ብፁዓን አበው ሊቃነ ጳጳሳት የቅዱስ ሲኖዶስ አባላት!

ጌታችን አምላካችንና መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ስለ ዘላቂው የቤተ ክርስቲያን ፈተና ሲነግረን ‹‹ወበዓለምሰ ሀለወክሙ ትርከቡ ሕማመ፤ በዓለም ሳላችሁ መከራ አለባችሁ›› እንዳለው ቤተ ክርስቲያን ከፈተና ተለይታ አታውቅም፤ ፈተናውም ከተወሰነ አቅጣጫ ብቻ የሚመጣ ሳይሆን ከብዙ አቅጣጫ ይከባታል፤ የቤተ ክርስቲያን መከራ ከውጭ ብቻም አይደለም ከውስጥም እንጂ፤ ከባዕድ ብቻም አይደለም ከወዳጅም እንጂ፣ የወዳጅ ፈታኝ እንደሚብስም ታውቆ ያደረ ነገር ነው፤ ባዕዳውያን አይሁድ ጌታን ይዘው የገደሉ የውስጥ ሰው የሆነው ይሁዳ በሰጣቸው ምልክት ነው፡፡

ከዚህ አንጻር የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን በአሁኑ ጊዜ በከባድ ፈተና ውስጥ እያለፈች ትገኛለች፤ እንደተነገረው የውጭው ፈተና ባይቀርላትም ከሱ በላይ ግን በውስጧ የሚነሡ ፈተናዎች ተልእኮዋን በአግባቡ እንዳትወጣ ዕንቅፋት ሆነውባታል፤ ከጥንት ጀምሮ የነበረ፣ በእግዚአብሔር ቃል የተቃኘ፣ የጸሊአ ሢመትና የጸሊአ ንዋይ መንፈሳዊ ባህሏ ተዘንግቶአል፤ በምትኩም ፍቅረ ሢመትና ፍቅረ ንዋይ ነግሦአል፤ መለያየትና መነቃቀፍ እየሰፉ መጥተዋል፣ ሃይማኖታችንንና ባህላችንን የማይወክሉ ኃይለ ቃላት፣ ኃላፊነት በጐደለው አገላለጽ እየተሰነዘሩ በጎቻችንን አስበርግገዋል፤ ድርጊቶቹ በበጎቻችን ዘንድ የነበረንን ተሰሚነትና ተደማጭነት ሊቀንሱብን እየተንደረደሩ ነው፡፡

እነዚህና እነዚህ የመሳሰሉ ክሥተቶች በውስጣችን ሥር በሰደዱ ቁጥር ጉዳትን እያስከተሉ ነው፤ ሰዎች ከኦርቶዶክሳዊ ቀኖና እና ሥርዓት ባፈነገጠ መልኩ ራስን በራስ የመሾም አባዜ እየተለማመዱ ነው፤ እሽቅድምድሙም በዚህ ዙሪያ አይሎአል፤ በአጠቃላይ የቆሮንቶስ ክርስቲያኖችን የፈተነ መለያየት በቤተ ክርስቲያናችንም ብቅ ጥልቅ እያለ እየፈተነን ነው፤ የፈተናው መንሥኤ ውጫዊ ሳንካ ባይጠፋበትም የውስጣችን ሰዎች ለሱ ምቹ ሆነው መገኘታቸው አልቀረም፤ በመሆኑም ቤተ ክርስቲያናችን በዚህ ፈተና የማይናቅ ጉዳት እየደረሰባት ነው፤ ከሁሉ በላይ ደግሞ ሰላምዋና አንድነቷ ጥያቄ ላይ ወድቆአል፡፡

ብፁዓን አበው ሊቃነ ጳጳሳት የቅዱስ ሲኖዶስ አባላት!

በሀብተ መንፈስ ቅዱስ ወልደን፣ በሀብተ ክህነት ሹመን፣ በመዐርገ ምንኩስና አልቀን በቤተ ክርስቲያን ኃላፊነት ያስቀመጥናቸው ሰዎች በውኑ ‹‹እርስ በርስዋ የምትለያይ ቤት… የሚለውን አምላካዊ አስተምህሮ እንዴት ዘነጉት? ወይስ ድሮውንም ሳያውቁት ነው ኃላፊነቱ የተሰጣቸው? ወይስ ደግሞ ሆን ብለው ቃሉን ቸል ብለውታል? ሁሉም ውሉደ ክህነት ለዚህ መልስ መስጠት ይጠበቅበታል፤ በመልካም አስተዳደርና በቂም በቀል እያሳበቡ ቤተ ክርስቲያንን ለማዳከም ብሎም ለማፍረስ መሮጥ በማናቸውም መመዘኛ ሚዛን አይደፋም፤ ውሃም አያነሣም፡፡
ችግር ሲኖር በመወያየት በጥበብና በሕግ ማረም እንጂ የጋራ ችግርን ለተወሰነ አካል በመለጠፍና እሱን ብቻ ተጠያቂ በማድረግ ንጹህ መሆን አይቻልም፤ ሁሉም ጓዳው ቢፈተሽ ከዚህ የተለየ ነገር አይገኝም፤ አንድነትንና ሰላምን ግቡ ያደረገ ግምገማን መገምገም፣ መወያየትና መመካከር፣ ሕግንና ሥርዓትን ማእከል አድርጎ መሥራት ተመራጭ መፍትሔ ነው፡፡

እንደሚታወቀው ባለፉት ዓመታት አስከፊ በደል ተፈጽሞአል አሁንም አልቆመም፤ ይሁን እንጂ በደል ዛሬ ብቻ የተጀመረ አድርገን አናስብ፤ ይብዛም ይነስ በደል ፊትም ነበረ፤ ዛሬም አለ፤ ነገም የተለየ ነገር ይኖራል ተብሎ አይታሰብም፡፡

በደልን በካሣና በዕርቅ በይቅርታና በምሕረት መዝጋት፣ ተመሳሳይ በደል እንዳይፈጸም አስተማማኝ የሆነ ተቅዋማዊ ሥርዓትን ማበጀት መልካም ፈሊጥ ይሆናል፤ በደልንና ጥፋትን ምክንያት አድርገን እስከ ዘለቄታው መለያየትን መምረጥ ግን ራስን በራስ መጉዳት ይሆናል፤ ስለዚህ ይህ ቅዱስ ጉባኤ በዚህ ዙሪያ በስፋትና በጥልቀት በመወያየት ሁሉንም ሊያስማማ በሚችል መልኩ ወደ ሰላምና ዕርቅ ሊያደርስ የሚችል ስራ መስራት ይኖርበታል፡፡

ብፀዓን አበው ሊቃነ ጳጳሳት የቅዱስ ሲኖስ አባላት!

የማኅበረ ሰባችን ችግር በቤተ ክርስቲያን ብቻ የተወሰነ አይደለም፤ በሀገር ደረጃ እየቀጠለ ያለው አለመግባባትም ለጠቅላላ ማኅበረ ሰባችን ፈተና ከሆነ ውሎ አድሮአል፤ የቤተ ክርስቲያናችን ፈተና ምንጭ ከሆኑትም አንዱና ዕድል ሰጩ ይህ ሀገራዊ አለመግባባት ነው፤ በዚህ አለመግባባት ምክንያት ገዳማውያን መነኮሳት፤ መምህራን ካህናት ምእመናን አብያተ ክርስቲያናት ከባድ ጉዳት ደርሶባቸዋል፤ በሰላም ወጥቶ መግባትም አጠራጣሪ ሆኖአል፤ ይህንን ችግር ለመፍታት የሚደረግ ጥረትም ጎልቶ አይታይም፡፡
በመሆኑም ይህ ክሥተት እውን ኢትዮጵያውያን የራሳችንን ችግር በራሳችን መፍታት የማንችል ሰዎች ነን ወይ? ለኛስ ከኛ የበለጠ ማን ይመጣልናል? የሚለውን ጥያቄ ልናነሣ ግድ ነው፤ ስለዚህ ለሀገር ህልውናና ድኅነት የሚበጅ ነገር እንዲመጣ ቤተ ክርስቲያን ባላት ሃይማኖታዊና ሰብአዊ ኃላፊነት ጠንክራ መስራት ይጠበቅባታል፤ ከዚህ በተረፈ ይህ ዓቢይ ጉባኤ ወሳኝና ወቅታዊ እንዲሁም ሐዋርያዊና ቀኖናዊ በሆኑ የቤተ ክርስቲያናችን ጉዳዮች ላይ ተወያይቶ ለቤተ ክርስቲያንና ለሀገር የሚበጁ ነገሮችን በማየት ጠቃሚ ውሳኔዎችን እንዲያሳልፍ በዚህ አጋጣሚ ለማሳሰብ እንወዳለን፡፡

በመጨረሻም
ዓመታዊው የርክበ ካህናት ቅዱስ ሲኖዶስ ምልአተ ጉባኤ በዛሬው ዕለት በእግዚአብሔር ፈቃድ የተጀመረ መሆኑን በመንፈስ ቅዱስ ስም እናበስራለን ፡፡

መልካም ጉባኤ ያደርግልን!
እግዚአብሔር አምላካችን ኢትዮጵያንና ሕዝቦቿን ይባርክ!!
ወስብሐት ለእግዚአብሔር!!!
አሜን፡፡

አባ ማትያስ ቀዳማዊ
ፓትርያርክ ርእሰ ሊቃነ ጳጳሳት ዘኢትዮጵያ
ሊቀ ጳጳስ ዘአክሱም ወዕጨጌ ዘመንበረ ተክለ ሃይማኖት
ግንቦት ፳፩ ቀን !፻0፮ ዓ.ም.
አዲስ አበባ፣ ኢትዮጵያ
ማኅበረ ቅዱሳን በተጨማሪ ማእከላት የደም ልገሳ መርሐ ግብር አከናወነ።


በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ሰንበት ትምህርት ቤቶች ማደራጃ መምሪያ ማኅበረ ቅዱሳን ከ ኢትዮጵያ የደም ባንክ ጋር በመተባበር ግንቦት 18 ቀን 2016 ዓ.ም የደም ልገሳ መርሐ ግብር በ25 ማእከላት ማከናወኑ ይታወሳል።

ይህ የደም  ልገሳ መርሐ ግብር ዛሬም በተለያዩ የማኅበሩ ማእከላት ላይ ቀጥሎ ውሏል።

ሰቆጣ፣ባሌሮቤ፣ዲላ እና ወሊሶ ማእከላት በዛሬው ዕለት የግቢ ጉባኤ ተማሪዎችን አባላትን እና ምእመናንን በማስተባበር የደም ልገሳ መርሐ ግብራትን አከናውነዋል።

ከመንፈሳዊ አገልግሎት በተጨማሪ በተለያዩ የማኅበራዊ ኃላፊነቶች ላይ ተሳትፎ እያደረገ የሚገኘው ማኅበረ ቅዱሳን ባከናወነው የደም ልገሳ መርሐ ግብር እጅግ በርካታ አባላት ተሳትፎ በማድረግ የብዙ ወገኖቻችንን ሕይወት መታደግ የሚችል ደም መለገስ ችለዋል።
የ፳፻ ፲ወ፮ ዓ.ም የርክበ ካህናት ቅዱስ ሲኖዶስ ምልዓተ ጉባኤ መግለጫ እንደሚከተለው ይነበባል።

በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን፡፡

ከኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን
ቅዱስ ሲኖዶስ የተሰጠ መግለጫ፡፡

በመንፈስ ቅዱስ የሚመራው የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ቅዱስ ሲኖዶስ በቅዱሳን አበው ሐዋርያት ትውፊት በፍትሕ መንፈሳዊ አንቀጽ 5 ቁጥር 164 በተደነገገው መሠረት ምልዓተ ጉባኤው የርክበ ካህናት መደበኛ ስብሰባውን ከግንቦት 21 እስከ ግንቦት 28 ቀን 2016 ዓ/ም ድረስ በርካታ አጀንዳዎችን በመቅረጽ ውይይት ሲያካሄድ ሰንብቷል፡፡

ምልዓተ ጉባኤው ለቤተ ክርስቲያናችን አንድነት፣ ለሐዋርያዊ ተልእኮ መስፋፋት፣ ለመንፈሳዊ ዕድገትና ለምእመናን ደኅንነት ትኩረት በመስጠት ለቅድስት ቤተ ክርስቲያናችንና ለሀገራችን ጠቃሚ የሆኑ ውሳኔዎችን አሳልፏል፡፡

በዚሁ መሠረት፡-

1.በቅድስት ቤተ ክርስቲያንና በሀገራችን መንግሥት መካከል ሊኖር ስለሚገባው መልካም የሥራ ግንኙነት በቅዱስ ፓትርያርኩ መሪነት ከመንግሥት የሥራ ኃላፊዎች ጋር የሚመካከር የብፁዓን አበው ሊቃነ ጳጳሳት ልዑክ ቅዱስ ሲኖዶስ ሰይሟል፤

2.በመላው ሀገራችን በተፈጠሩ ግጭቶች፣ አለመግባባቶችና የሰላም ዕጦት በርካታ የሰው ሕይወት መጥፋትና የንብረት ውድመት እንደቀጠለ መሆኑ ቅዱስ ሲኖዶስን በእጅጉ አሳዝኗል፡፡ ስለዚህ ጉዳዩ የሚመለከታቸው ሁሉም ባለድርሻ አካላት ከግጭትና ከጥፋት ድርጊት ተቆጥበው የተፈጠረውን አለመግባባትና ግጭት በውይይትና በምክክር እንዲፈቱ እና ዘላቂ ሰላም እንዲረጋገጥ ቅዱስ ሲኖዶስ በአጽንኦት ጥሪውን ያቀርባል፤
3.በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር እየተከናወነ ባለው የኮሪደር ልማት ምክንያት ለፈረሱ የቤተ ክርስቲያናችን ይዞታዎች የከተማ አስተዳደሩ ምትክ ቦታ በመስጠትና ቤተ ክርስቲያናችን ወደ መልሶ ማልማት እንድትገባ ድጋፍ በማድረግ፤ በተለይም ክብርት ከንቲባ ወ/ሮ አዳነች አበቤ በፈረሰው የጽርሐ ምኒልክ የቤተ ክርስቲያኒቱ ሕንፃ ምትክ በከተማ አስተዳደሩ ሙሉ ወጭ ተጨማሪ ምድር ቤትና የቦታ ስፋት ያለው B+G+4 ሕንፃ ገንብቶ ለማስረከብ ቃል በመግባትና የቤተ ክርስቲያናችን የበላይ ኃላፊ አባቶች በተገኙበት የመሠረት ድንጋይ እንዲጣል ማድርጋቸውን ቅዱስ ሲኖዶስ ከምስጋና ጋር የተቀበለው ሲሆን በተሰጠን ምትክ ቦታ ላይም የከተማው ፕላን በሚፈቅደው መሠረት የመልሶ ማልማት ሥራው እንዲከናወን ቅዱስ ሲኖዶስ ወስኗል፡፡

4.የሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን ከተቋቋመበት አዋጅ መረዳት እንደሚቻለው ባለድርሻ አካላትን ባሳተፈ ሁኔታ ሀገራዊ ችግሮችን በምክክርና በውይይት ለመፍታት የተቋቋመ መሆኑን ተረድተናል፡፡ ይሁን እንጅ ሀገረ መንግሥትን ከመመሥረት ጀምሮ በአስታራቂነትና በሰላም ግንባታ ግንባር ቀደም ተጠቃሽ ለሆነችው እናት ቤተ ክርስቲያን እስከአሁን ድረስ በይፋ የቀረበ የተሳትፎ ጥሪ ሳይኖር ኮሚሽኑ የተሳታፊ ልየታንና አጀንዳ መረጣ አጠናቆ ወደ ምክክር ትግበራ እየገባ መሆኑ ቅዱስ ሲኖዶስን ቅር አሰኝቷል፡፡ በመሆኑም የቤተ ክርስቲያኒቱ ተሳትፎና አጀንዳ የማቅረብ መብቷ እንዲረጋገጥ ከኮሚሽኑ ጋር በመነጋገር ጉዳዩን ተከታትሎ ለፍጻሜ የሚያበቃ ኮሚቴ ቅዱስ ሲኖዶስ ሰይሟል፡፡

5.የብፁዓን አባቶች የዝውውርና የአህጉረ ስብከት ሥያሜን አስምልክቶ የቀረቡ ጥያቄዎችን ምልዐተ ጉበኤው ተመልክቶ ተገቢውን ውሳኔ አሳልፏል፤

6.የሃይማኖት ጉዳዮች ረቂቅ አዋጅ ላይ ቅዱስ ሲኖዶስ በሰፊው ከተወያየ በኋላ በረቂቅ አዋጁ ሊሻሻሉ ይገባቸዋል ብሎ ያመነባቸውን የማሻሻያ ሐሳቦች በማዘጋጀት ለሚመለከተው መንግሥታዊ ተቋም እንዲላክና ረቂቅ አዋጁ ከመጽደቁ በፊት የተሰጡት የማሻሻያ ሐሳቦች በረቂቁ ስለመካተታቸው ክትትል የሚያደርግ ኮሚቴ ቅዱስ ሲኖዶስ ሰይሟል፡፡

7.በቅዱሳት መጻሕፍት ላይ ተመሥርቶ አባታዊ ምክርና ተግሣጽ ማስተላለፍ ከቀድሞ ጀምሮ የነበረ መጽሐፍ ቅዱሳዊ መሠረት ያለው መሆኑ ቢታወቅም በሀገራችን ኢትዮጵያ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በተፈጠሩ አለመግባባቶች የተከሰቱትን ወቅታዊ ችግሮች አስመልክቶ እየተላለፉ ያሉ ቤተ ክርስቲያንን የማይወክሉ መልእክቶችን ቅዱስ ሲኖዶስ የማይቀበላቸውና በጥብቅ የሚቃወማቸው መሆኑን እየገለጸ ወደፊት እንዲህ ዓይነት ተመሳሳይ ድርጊት እንዳይፈጸም ለማድረግ ይቻል ዘንድ ወጥ የሆነ የመግለጫ አሰጣጥና የትምህርተ ወንጌል ተልእኮ ሕገ ደንብ ተዘጋጅቶ ለምልዐተ ጉበኤ እንዲቀርብ ቅዱስ ሲኖዶስ ወስኗል፤

8.ግብረ ሰዶማዊነትና የተመሳሳይ ጾታ ጋብቻ በሕገ ተፈጥሮም ሆነ በሰው ልጅ የሰብዓዊ አኗኗር ፈጽሞ ተቀባይነት የሌለው፣ ፈጣሬ ዓለማት እግዚአብሔር መለኮታዊ ፈቃዱ በተገለጠባቸው ቅዱሳት መጻሕፍት ፈጽሞ የተከለከለ፣ በቀኖናተ ቤተ ክርስቲያን፣ በፍትሕ መንፈሳዊና በፍትሐ ብሔር ድንጋጌዎች፣ በሥነ ልቦና ደንቦች የተወገዘ፣ ሥነ አእምሮዊ ሚዛንን የሚያዛባ፣ ግለሰባዊ ማንነትን፣ ቤተሰባዊ ሕይወትን፣ ማኅበራዊ ትሥሥርን የሚጎዳ ተግባር በመሆኑ ቅዱስ ሲኖዶስ እያወገዘ የተመሳሳይ ጾታ ጋብቻና የግብረ ሰዶማዊነትን ኃጢአት በተመለከተ የቅድስት ቤተ ክርስቲያንን አቋም በሚገልጽ መልኩ ራሱን ችሎ ዓለም አቀፋዊ ይዘቱን ባገናዘበ ሁኔታ ዝርዝር መግለጫ እንዲሰጥ ቅዱስ ሲኖዶስ ወስኗል፤

9.በደቡብ የሀገራችን ክፍል የቤተ ክርስቲያኒቱን አብነት ትምህርት ከማስፋፋትና ከፍ ያለ መዐርግ ከመስጠት አንፃር የጋሞና አካባቢው ዞኖች ሀገረ ስብከት የዝጊቲ ደብረ ሰላም አቡነ ገብረ መንፈስ ቅዱስ ቤተ ክርስቲያን የአራቱ ጉባኤያት ማስመስከሪያ ትምህርት ቤት እንዲሆን በቀረበው ጥናት መሠረት ቅዱስ ሲኖዶስ ለምሥክር ጉባኤ ቤቱ ዕውቅና በመስጠት ወደ ትግበራ እንዲገባ ወስኗል፡፡

10.ከሀገራችን ውጭ ባሉ አህጉረ ሰብከት መደበኛ አገልግሎት ለመስጠት የሚላኩ አገልጋዮች በክፍሉ ሊቀጳጳስ ሲጠየቅ በሙያ ብቃታቸው፣ በምግባራቸውና በመንፈሳዊነታቸው የተመሰከረላቸው አገልጋዮች ከሁሉም አህጉረ ስብከት በብፁዓን ሊቃነ ጳጳሳት አቅራቢነት በውድድር እየተለዩ በቋሚ ሲኖዶስ ውሳኔ እንዲላኩ ቅዱስ ሲኖዶስ ወስኗል፡፡

11.የቅድስት ቤተ ክርስቲያን አስተዳደር ዘመኑን የዋጀ እንዲሆን ቅዱስ ሲኖዶስ የዐሥር ዓመት መሪ ዕቅድ በማጽደቅ ወደ ትግበራ እንዲገባ መወሰኑ ይታወሳል፡፡ በዚሁም መሠረት ለአፈጻጸሙ ያመች ዘንድ በባለሙያዎች ተዘጋጅቶ የቀረበውን መዋቅራዊ አደረጃጀት በማጽደቅ በሕገ ቤተ ክርስቲያኑና በቃለ ዓዋዲው ተካቶ ሥራ ላይ እንዲውል ቅዱስ ሲኖዶስ ወስኗል፡፡

12.በመንበረ ፓትርያርክ ጠቅላይ ቤተ ክህነት ጽ/ቤት ተዘጋጅቶ የቀረበውን የ2017 ዓ.ም. ዓመታዊ በጀት በማጽደቅ በሥራ ላይ እንዲውል ቅዱስ ሲኖዶስ ወስኗል፡፡

በአጠቃላይ ቅዱስ ሲኖዶስ በመንፈስ ቅዱስ እየተመራ ላለፉት ተከታታይ ቀናት በመንፈሳዊ፣ ማኅበራዊና ሀገራዊ ጉዳዮች ላይ በመወያየትና ተገቢውን ውሳኔ በማስተላለፍ መደበኛ ስብሰባውን በዛሬው ዕለት በጸሎት አጠናቅቋል፡፡ መሐሪና ሁሉን ቻይ የሆነ እግዚአብሔር አምላካችን ለሀገራችን፣ ለሕዝባችን፣ ለዓለሙ ሁሉ ሰላሙን፣ ፍቅሩንና አንድነቱን ይስጥልን፡፡
እግዚአብሔር ኢትዮጵያንና ሕዝቦቿን ይባርክ
ወስብሐት ለእግዚአብሔር አሜን

አባ ማትያስ ቀዳማዊ
ፓትርያርክ ርእሰ ሊቃነ ጳጳሳት ዘኢትዮጵያ ሊቀ ጳጳስ ዘአክሱም
ወዕጨጌ ዘመንበረ ተክለ ሃይማኖት

ግንቦት ፳፱ ቀን ፳፻፲፮ ዓ.ም. ኢትዮጵያ አዲስ አበባ
2024/06/06 17:54:30
Back to Top
HTML Embed Code: