Telegram Group Search
✥ሰንበት ተሽራለችን?✥

• ጥያቄ:-
- ኤፌ 2 ÷15 «.... በአዋጅ የተነገሩትንም የትዕዛዛት ሕግ ሽሮ….»
- ዕብ 7÷19-22 «….ስለዚህ የምትደክም የማትጠቅምም ስለሆነች የቀደመች ትዕዛዝ ተሽራለች…..»
- ዕብ 8 ÷7-13 «….ፊተኛው ኪዳን ነቀፋ ባይኖረው ለሁለተኛው ስፍራ ባልተገለኘም ነበር…»
- ዕብ 10 ÷10 «...ሁለተኛውን ሊያቆም የፊተኛውን ይሽራል…»
- ዮሐ 5 ÷18 «... እንግዲህ ሰንበትን ስለሻረ ብቻ አይደለም… »
- ዕብ 4÷9 « ...እንግዲያስ የሠንበት እረፍት ለእግዚአብሔር ሕዝብ ቀርቶላቸዋል…»
እነዚህ ከላይ የዘረዘርኳቸው ጥቅሶች ሰንበትን እንዳንዳድ የብሉይ ሕጎች እንደተሸሩ ይናገራሉ፡፡ የተሻሩት ሕጎች የትኞቹ ናቸው ወይስ የተሻረ ሕግ የለም ካልተሸረ ለምን እነዚህ ጥቅሶች ተጠቀሱ?

• መልስ:- በመጀመሪያ ከላይ የተዘረዘሩት የሰንበትን መሻር አይደለም የሚያመለክቱት የተሻሩት ሕጎች የትኞቹ ናቸው ካልክ ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ብፁዓን ብፁዓን ብሎ ሲያስተምር አይሁዳውያን ህግን የሻረ አድርገው ሲያስቡ ጌታችን ፈቃዳቸውን አውቆ እንዲህ በማለት ነበር የገለጸላቸው «ሕግንና ነቢያትን ለመሻር የመጣሁ አይምሰላችሁ ልፈጽም እንጂ ለመሻር አልመጣሁም እውነት እላችኋላሁ ሰማይና ምድር እስኪያልፍ ድረስ ከሕግ አንዲት የመጣ ወይም እንዲት ነጥብ ከቶ አታልፍም »፡፡ ማቴ 5 ÷17 -18 በማለት ሊሽር ሳይሆን ሊያጸና እንደሆነ ገለጾላቸዋል።

- ከሕግ አንዲት ነጥብ ከምትሻር ይህ ዓለም ቢያልፍ እንደሚሻል «ከሕግ አንዲት ነጥብ ከምትወድቅ ሰማይና ምድር ሊያልፍ ይቀላል» ሉቃ 16 17 እንዲሁም ከአስርቱ ትዕዛዛት አንዲቱን የሻረ ሁሉን እንደሻረ እንደሚያሰኝበት ቅዱስ ያዕቆብ በመልእክቱ «ሕግን ሁሉ የሚጠብቅ ነገር ግን በአንዱ የሚሰናከል ማንም ቢኖር በሁሉ በደለኛ ይሆናል» ያዕ 2 ÷10 በማለት ገልጾልናል፡፡ ታዲያ እንዲ ከሆነ የተሸረው ሕግ የተባለው የትኛው ነው ለተባለው ሊመጣ ላለው ምሳሌ ጥላ የነበረው በአማናዊ የተተኩትን ነው ፡፡ ከእነዚህም ጥቂቶቹ መካከል፦

- መሥዋዕተ ኦሪት፦ ለሥርየተ ኃጢአት የሚቀርበው የነበረው የኦሪት መሥዋዕት በክርስቶስ አማናዊ ቅዱስ ሥጋና ክቡር ደሙ ተተክቷል፡፡

- ግዝረት፦ በአመኑት እና ባላመኑት መካከል መለያ ምልክት የነበረው የግዝረት ሕግ በጥምቀት ተሽሯል፡፡ ዛሬ ለማመናችን ብንገዘርም ባንገዘርም ምንም አይጠቅመንም፡፡

- የኦሪት ክህነት፡- ይህ ደግሞ ከነገደ ሌዊ ብቻ የነበሩ ሲሆን ከሌላ ነገድ የነበረ የክህነትን አገልግሎት ሊፈጽም የማይችል የነበረው ዛሬ ግን በዘር በነገድ ያልሆነ የክህነት ሥርዓቱ በሚያዘው መሰረት ለዚያ ብቁ የሆነ ከወንዶች ሊሾም ይችላል፡፡

- በድን የነካ ርኵስ የሚባል የነበረ ፦ ዛሬ ግን በክርስቶስ ክርስቲያን የተባለው የመንፈስ ቅዱስ ቤት ስለሆነ ርኵስ አይባልም ይልቁንም አጥበን ገንዘን ስመን ሽቱ ቀብተን በክብር የምንፈጽም ስለሆነ እንደ ቀድሞ ርኵስ አንሰኝም፡፡ ለምን በጥምቀት በቊርባን ያገኘነው የልጅነት ጸጋ ከነፍስ ከሥጋችን አይለይምና ተመልሶልናልና፡፡ እንዲሁም እንደ ቀድሞ የነፍስ ከሥጋ መለየት የምንፈራው ሳይሆን ይልቁንም የነፍስ ከሥጋው መለየት ኃጢአትን ከመሥራት እንደመራቅ እንቆጥረዋለን፡፡ የምንፈራው ሞት ግን ከእግዚአብሔር መለየት ነው፡፡

- የወለደች ሴት የሚፈጸመው የነበረው የመንፃት ሕግ ይህ ተሽሯል፦ ይህ ማለት ደግሞ የወለዱት ሴቶች 40 እና 80 ቀናቸው ሳይፈፀም ቤተመቅደስ ውስጥ ይገባሉ ማለት አይደለም እንዲሁም ከባለቤታቸው ጋር ሩካቤ ሥጋም ይፈጽማሉ ማለትም አይደለም፡፡ ነገር ግን ቀድሞ እንደ መርገም ወራት እርኩስ ናት ማለት ቀርቷል ፡፡ ለመንፃቷም የምታቀርበው የነበረው መስዋዕት ተሸሯል፡፡ ባጠቃላይ የተሻሩት ሕግ የተባሉት በጥቂቱ ይህን ሲመስሉ ሌሎችም አሉ፡፡


ከላይ የተዘረዘሩት ጥቅሶች ምንን ያመለክታሉ ለሚለው ሰፋ ያለ ትንታኔ የሚያስፈልጋቸው ቢሆኑም በጥቂቱ እንመልከት፡፡

• «በአዋጅ የተነገሩትን የትዕዛዝን ሕግ ሽሮ » ኤፌ 2 ÷15 በዚህ ምዕራፍ ከተጠቀሰው ቁጥር በላይ ያለውን ጨምረህ ብናነበው ምን ለማለት እንደፈለገ እንረዳዋለን፡፡

- ምን ጊዜም መጽሐፍ ቅዱስን ስናነብ ከላይ አርዕስቱን ዐይተን እንደሆነ ኅዳጉን ማየት ኅዳጉን 0ይተን እንደሆነ አርዕስቱን ማየት ይጠበቅብናል፡፡ ለምሳሌ አርዮስ ጥበብ ጌታ እግዚአብሔር ፈጠረኝ ያለውን 0ይቶ ክብር ምስጋና ይግባውና ጌታን ፍጡር አለው፡፡ ዝቅ ብሎ ኅዳጉን ቢያይ ግን ቅድመ ዓለም ከአካሉ አካል ከባህሪይው ባህሪይው እንደተወለደ « ተራሮች ሳይመሰረቱ ከኮረብቶች በፊት ወለደኝ» ሲል ያገኘው ነበር፡፡ ስለዚህ መጽሐፍትን ስናነብ አንድ ጥቅስ ብቻ ይዘን ስንጎዳ እንዳንገኝ የምናነበውን ልናስተውለው ይገባል፡፡

- ወደ ጥቅሱ እንመለስ «በአዋጅ የተነገሩትን የትዕዛዝ ሕግ ሽሮ » የተባለው የተገዘረ ያልተገዘረ ተብሎ የተነገረው ሕግ ያመነ የተጠመቀ በሚለው መሻሩን በሐዲስ ኪዳን አይሁዳዊ ግሪካዊ ተብሎ የማይለይ መሆኑና በክርስቶስ በማመን አንድ እንደሚሆኑ የሚያመለክት ነው፡፡
• ዕብ 7÷18 -22 «…. ስለዚህ የምትደክም የማትጠቅምም ስለሆነች የቀደመች ትዕዛዝ ተሽራለች…..» የቀድሞ መስዋዕት አቅራቢውም መስዋዕቱም ሕፀጽ ያለባቸው ፍጹምም ሥርየተ ኃጢኣት የማያሰጥ ነበሩ ፡፡ መስዋዕት አቅራቢውም የተባለው ሊቀ ካህኑም ደካማ ነበር፡፡ በመጀመሪያ ለራሱ ኃጢአት መሥዋዕት አቅርቦ ነበር ለሕዝቡ መስዋዕት የሚያቀርብ የነበረው፡፡ ስለዚህም ደካማ ነበረው በሚያቀርበውም መስዋዕት አፍአዊ ሥርየትን ቢያሰጥ እንጂ ውስጣዊ ሥርየትን የሚያስጥ አልነበረም፡፡

ለዚህም ነው የቀደመው የሥጋ የተሠራ ሕግ ያለው ቅዱስ ጳውሎስ ስለዚህም የምትደክም የማትጠቅምም ስለሆነች የቀደመች ትዕዛዝ ተሽራለች ያለው መሻርዋም ነውር ነቀፋ በሌለበት ንጹሐ ባህሪዩ እርሱን መስዋዕት አድርጎ በማቅረብ ፍፁም ሥርየተ ኃጢአትን እንደሰጠንና ዛሬም መሰዋዕት አቅራቢው እራሱ መስዋዕቱ እራሱ ይቅር ባዩም እራሱ ነውና የፊተኛውን የኦሪቱን በማሳለፍ ኋላኛውን ተካ ፡፡ ነቀፋ የነበረበትን ነቀፋ በሌለው መተካቱን ሲያጠይቅ ነው ቅዱስ ጳውሎስ የጠቀሰልን፡፡

• ሌላው ሰንበት እንደተሻረ ያመላክትልና ለማለት ከሚነሡ ጥቅሶች መካከል «እንግዲህ ሰንበትን ስለሻረ ብቻ አይደለም » የሚለውን ነው። ዮሐ 5 ÷18 « ...እንግዲያስ የሠንበት እረፍት ለእግዚአብሔር ሕዝብ ቀርቶላቸዋል…»ዕብ 4÷ 9

- እነዚህ ሁለቱም ቀዳሚት ሰንበት ስለመሻርዋ የሚያመለክቱ አይደሉም በዮሐንስ ወንጌል ላይ የተጠቀሰው አይሁዶች ስለመሰላቸው ነው እንጂ ጌታ ሰንበትን ስለመሻሩ የሚያመለክት አይደለም እንዲት ሕግን ልፈጽም መጣሁ እያለ እንዴት ሻረ እንለዋለን፡፡

- ሰንበት የሚቀድሰን እሱ እንደሆነ ምልክት ናት «እኔ የምቀድሳችሁ እግዚአብሔር እንደሆንኩ ታውቁ ዘንድ በእኔና በእናንተ ዘንድ ለልጅ ልጃችሁ ምልክት ነውና ሰንበቴን ፈጽሞ ጠብቁ» ዘፀ 31÷13

- በሌላም በኩል ይህ ዓለም ካለመኖር ወደ መኖር ያመጣ አንድ እግዚአብሔር እንዳለና ከድካማችን የሚያሳርፈን ፈጣሪ እንዳለንና ኋላም የማታልፍ ጣር ጋር ድካም የሌለባት መንግስተ ሰማያት እንደሚያወርሰን ተስፋችን የምንገልጥበት ናት፡፡

. ሰንበት የመቀደሳችን ምልክት እና የመንግሥተ ሰማያት ዕረፍት ምሳሌ ከሆነች እንዴትስ ተሻረች ይባላል፡፡
- ጌታችን በሰንበት ሰውን ጤነኛ በማድረግ በሰንበት ሊደረግ የሚገባውን ነው ያስተማረን እንዲሁም ሰንበት ስለ ሰው ተሠራች እንጂ ሰው ስለሰንበት አለመሆኑን ገለጸልን፡፡ ቅዱስ ያሬድም «ሠርግ ሰንበተ ለእረፍተ በአፍቅሮተ ሰብእ» እንዳለ ።

- ስለዚህ በዮሐ 5፥18 ላይ የተገለጸው አይሁድ የመሰላቸው የሰንበት ትርጉም ስላልገባቸው ሲሆን፥ በዕብ 4፥9 ላይ ደግሞ ቅዱስ ጳውሎስም ለዕብራውያን በላከው መልዕክቱም ፍጹም እረፍት የሚሆነው በመንግስተ ሰማያት እንደሆነ ሲያጠይቅ ነው፡፡

✍️ አምኃ ሥላሴ / መኩሪያ ተስፋዬ

https://m.facebook.com/mekuria.tesfaye.71

https://youtube.com/channel/UC8v52_jNY156sxZtplafDtw (የዩቱብ አድራሻ)
✔️ ይህ ጾም ኢትዮጵያን ሲያገለግል የኖረ ጾም ነው :: ለምሳሌ :-
- የአድዋ ጦርነት በዚህ ጾም ላይ ነበር፦
ሠራዊቱ ወደ ጦር ሜዳ ሄደናል ብለው ጾም እየገደፈ ሳይሆን ጥራ ጥሬ እየበሉ ነው የተዋጉት

- ኋላም በአጼ ኃይለ ሥላሴ ዘመንም የማይጨው ጦርነት በ0ቢይ ጾም ነው ነገር ግን እንደአድዋ ጦርነት ሳይሆን የተቀላቀለ ጾም እየገደፉ ስለዘመቱ እንደቀድሞው ያህል ኃይል አልተገኘም :: ቢሆንም 5 ዓመት ያህል ክርስቲያኑ ሕዝብ ከእግዚኣብሔር ጋር ታግሎ ለድል በቅቷል ንጉሡም ከተሰደዱበት ለሃገራቸው በቅተዋል።


- በ66 ዓመተ ምህረትም የነበረው ጦርነት በ0ቢይ ጾም ጊዜ ነበረ (የካቲት ማሪያም ተጀመረ) ነገር ግን እግዚአብሔር ምን ሠራችሁ እንጂ ምን በላችሁ አይልም የሚሉ መናፍቃን የበዙበት ጊዜ ስለ ነበር እጅግ አስቸጋሪ ሆኗል::
(ሊቀ ጠበብት አለቃ አያሌው ታምሩ)
እኛ የሕይወት ወንጌል ተማርንባችሁ
ጌታ ሆይ አንተ ግን መዳን ለዚህ ቤት ይሁን በል
ውዶች ሆይ እናንተም ለጌታ ማዳኑ ምክንያት ለመሆን ተመልክታችሁ የተቻላችሁን አድርጉ
https://youtu.be/947NmY1Sq58?si=vXcU90sy_F-Ec2Tw
#ምኩራብ
-> የዐቢይ ጾም ሦስተኛ ሣምንት ምኩራብ ይባላል።

-> ምኵራብ ፦ የአይሁድ መቅደስ ቤተ ጸሎት ታላቅ አዳራሽ ነበር።

-> በዚህ ሣምንት ጌታ በመዋዕለ ስብከቱ፡ በምኩራብ ገብቶ ማስተማሩ ይነገራል (ማቴ 4፥23 ማር 1÷21 ሉቃ 4÷15)

-> ክርስቶስ ለማስተማር በገባ ጊዜ አይሁድ ቤተ ጸሎቱን እንደ ስያሜው ሳይሆን መሸጫና መለዋወጫ መገበያያ አድርገውት ስለአገኛቸው ቤቴ የጸሎት ቤት ትባላለች እናንተ ግን የወንበዴዎች ዋሻ መሸጫ መለዋወጫ አደረጋችሁት ብሎ ሰዎችንና እንስሳትን በጅራፍ እየገረፈ ገበታቸውን እየገለበጠ አባሮአቸዋል ስለዚህ ይህ ሳምንት ለታሪኩ መታሰቢያ ምኩራብ ተብሉአል (ማቴ 21፥12-13
ማር 11፥15-18:: ሉቃ 19÷45-47 ዮሐ 2÷14-16)

-> ቅዱሳን ሐዋርያትም እንደ ጌታችን ለጸሎትና
ለትምህርተ ወንጌል ወደ ምኩራብ ይወጡ ነበር፡፡ የሐዋ 3፥1። የሐዋ.13፥5:: የሐዋ.14፥1:: የሐዋ.17-1:: የሐዋ.10-17:: የሐዋ.18-4:: የሐዋ.19፥8)


-> ምኩራብ ፦ ለአምልኮና ለትምህርት ለሕብረተሰቡም ጠቅሞአል

-> ምኩራብ በአለቆች ይመራ ነበር (ማር 5፥ 22፡፡ የሐዋ 3÷14-15:: የሐዋ18፥8)

-> በየሳምንቱ ሕዝቡ ሁሉ በምኩራብ ይሰበሰቡ ነበር፡፡ (ሉቃ 4÷16፡፡ የሐዋ.15 21)፡፡

-> ወንዶችና ሴቶች ለየብቻቸው ይቀመጡ ነበር።

->የእግዚአብሔር ቃል ሲነበብ አንባቢው እንዲሰማ በተዘጋጀው ከፍተኛ ቦታ ይቆም ነበር::
የክብር ወንበሮች ከዚህ ቦታ ፊት ለፊት ነበሩ (ማቴ 23÷6:: ሉቃ 4፥20)

መዝሙር ዘምኩራብ :-
ቦአ ኢየሱስ ምኩራቦሙ ለአይሁድ

ምንባባት ምኩራብ ዘቅዳሴ :-
- ቆላ 2÷16-ፍም፡፡
- ያዕቆብ 2፥14-ፍም::
- ግ.ሐዋ 10፥1-9

ምስባክ ፦
" እስመ ቅናተ ቤትከ በልዐኒ ትዕይርቶሙ ለእለ ይትዔየሩከ ወድቀ ላዕሌየ ወቀጻዕክዋ በጾም ለነፍስየ " (መዝ 68፥9)

ወንጌል ዮሐ 2፥12-ፍም

ቅዳሴ ዘእግዚእነ (ነአኩተከ)


✍️ አምኃ ሥላሴ / መኩሪያ ተስፋዬ 

https://m.facebook.com/mekuria.tesfaye.71

https://www.youtube.com/channel/UC8v52_jNY156sxZtplafDtw/about (የዩቱብ አድራሻ)
" ብዙ ሰዎች አንዳቸው ለሌላቸው የጾሙ ግማሽ አለፈ ግማሹን ጾም ፈጽመናል' ሲባባሉ እመለከታለሁ እኔ ግን እንዲህ ያሉት ሰዎች የጾሙ ግማሽ በማለቁ በዚህ እንዳይደሰቱ እመክራቸዋለሁ ከዚህ ይልቅ በጾማቸው የኃጢአታቸው ግማሽ ተወግዶ ስለ መሆኑ እንዲያስቡናበእርግጥ በጾማቸው እንደዚህ ዓይነት ጥቅም አግኝተው ከሆነ ያን ጊዜ ቢደሰቱ መልካም ይሆናል ልናስብበት የሚገባው ነገር ይህ ነውና፣ ጾመን ስንጨርስ ልክ ስንጀምር እንደ ነበርነው ዓይነት ሰዎች ሆነን ሳይሆን ከኃጢአታችን የነጻን ሰዎች ሆነን እንድንጨርሰው መሆንን ነው የክረምት ጠቀሜታው የበለጠ የሚታወቀው ወቅቱ ካለፈ በኋላ ነውና ያን ጊዜ የአበባዎች ማበብ የአዝመራው ማፍራት የዛፎች መለምለም እነዚህ ሁሉ በመታየታቸውና በመውጣታቸው ከክረምቱ ያገኙትን ጠቀሜታ በግልጽ ይናገራሉ፡፡ በእኛም እንዲሁ ይሁን፡፡ በጾም ወራት ያገኘነው መንፈሳዊ ጥቅም ጾመ ካለፈ በኋላ በእኛ ላይ በሚያፈራው መልካም ፍሬ ጠቀሜታው ግልጽ ሆኖእንዲታይ ይሁን፡፡ እንዲህ ካደረግን ጾመ እንደገና ተመልሶ ሲመጣ በደስታ እንቀበለዋለን፡፡
ከጾም የሚገኘውን ጥቅም በትክክል የተረዳነውና በጾማችን ወቅት ያንን ጠቀሜታየምንቀስመው ሆነን ቢሆን ኖሮ ጸሙበየቀኑ እንዲመጣ በተመኘን ነበር፡፡ እንዲህ ሆኖም የጾሙንመምጣት መናፈቃችንንና ለጾም ያለንን ጉጉትና ናፍቆት መቀነስ የለብንም፡ እርሱን በማሰብመፍራትና መጨነቅም አይኖርብንም፡፡”
(ቅዱስ ዮሐንስ አፈ ወርቅ፣ ትምህርት በእንተ ምክንያተ ሐውልታት 18 ቁ. 1-2)
"የጠላቱን ከተማ ለመቆጣጠር የዘመተ ንጉሥ አስቀድሞ የውኃውን መንገድ ይዘጋል፤ የእህሉንም መግቢያ ይይዛል። ያን ጊዜ ጠላቶቹ ይራባሉ ይጠማሉ። የነፍስን ፆር ለማሸነፍም በተመሳሳይ መንገድ መጠቀም ይገባል። አንድ ሰው በጾምና በረሃብ ከጸና የነፍሱ ጠላቶች ይደክማሉ።"
(ቅዱስ ዮሐንስ ሐፂር)
#መጻጒዕ

-> የ0ቢይ ጾም አራተኛ ሣምንት መጻጕዕ ይባላል።

-> ፀግ0 ፤መጸጕዕ ፦ በቁሙ ጎባጣ በጀርባው ላይ እንደ ሻኛ ያለው ደረቱ ከጉልበቱ የተጠጋ ሕመምተኛ በሽተኛ ማለት ነው።

-> በዚህ ሣምንተ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ድውያንን መፈወሱን ዕውራንን ማብራቱን የሚያነሳ መዝሙር ይዘመርበታል፡:

ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ለጌትነቱ ምልክት በሕዝቡ ያሉ ድውያንን ሁሉ ይፈውስ ነበር፡። የተአምራቱም ዜና በሶርያ በአራቱ ማዕዘን ደረሰ ተብሎ በተነገረው መሠረት ቅዱስ ማቴዎስ 4፥23-25 አንደጻፈው ቀጥለን እናያለን በማቴ 8 ፥1-4 ከተራራ በወረደ ጊዜ ብዙ ሕዝብ ተከተሉት ለምጻም ቀርቦ ጌታ ብትወድስ ልታነፃኝ ትችላለህ እያለ ሰገደለት እጁንም ዘርግቶ ዳሰሰውና ንፃ አለው ወዲያውም ለምፁ ነፃ
- በምዕ 8፥5-13 የመቶ አለቃውን ልጅ በቃሉ ፈወሰ፣ የጴጥሮስ አማት ከንዳድ ፈወሳት
- በምዕ 8 ፥14 አጋንንት አወጣ በምዕ 8፥16ና በ8፥28 በዚህ ተአምራት የምንረዳው ቁም ነገር
ሰስዎች ያደሩ አጋንንት ክርስቶስን የእግዚአብሔር ልጅ ብለው ማመናቸውን ነው:: የሐዋ 19÷15:: ያዕ 2÷19::

-> ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ የፈወሳቸው ህሙማን ብዙ ሲሆኑ ለምሳሌ ያህል ከላይ በጠቀስነው በማቴዎስ ምዕራፍ 8 ያሉትን እንዳዳነ ሁሉ በሌሎች ወንጌላውያን ምዕራፍና ቁጥርም በርካታ በሽተኞችን እንደፈወሰ ተገልጿል ከተፈወሱት ሰዎች መካከል የኻያ ሦስቱ ታሪክ ተገልጦአል ከእነርሱ ሌላ ኢየሱስ ሦስት ሙታንን አስነስቶአል አንደኛ የኢያኢሮስን ሴት ልጅ (ማቴ 9፥18-26) ሁለተኛ
የመበለቲቱን ልጅ ፈወሳት (ሉቃ 7÷11-17) ሦስተኛውም ደግሞ አልዓዛር (ዮሐ 11፥43-44)፡፡

-> ክርስቶስ በአምስት አይነት መንገድ ህሙማን ፈወሰ
1- በቃሉ (ማቴ8፥16፡፡ ዮሐ 4÷50)
2- በመዳሰስ (ማቴ 8፥} ፣ ሉቃ 5÷13)
3- እጅ በመጫን(ማር 6፥5፣ 8፦22)
4- ጭቃን በመቀባት (ዮሐ 9÷6-7)
5- በልብሱ ጫፍ (ማቴ9፥20፡፡ 14፥36)

-> እግዚአብሔር ፈዋሽ ነው (ዘጸ 15፥26) ፈዋሽነቱ ለሁሉ ቢሆንም በሰፊው የሚነገረው ግን በዮሐ 5÷5-15 ያለ በሽተኛ ነው::
ይኸውም ኋላ ጌታችን ኢየሱስን በጥፊ የመታው ነው ብለው ሊቃውንት ይተረጉማሉ (ዮሐ 18፥22)::

መዝሙር ዘመፃጉዕ አምላኩስ ለአዳም

ምንባብ ዘቅዳሴ
- ገላ 5፥1-ፍም::
- ያዕ 5፥14-ፍም::
- ግሐዋ 3÷1-12

"ምስባክ እግዚአብሔር ይረድኦ ውስተ አራተ ሕማሙ ወያመይጥ ሎቱ ኩሎ ምስካቤሁ እምደዌሁ አንዕ እቤ እግዚኦ ተስሐለኒ " (መዝ 40፥3)

ወንጌል ዮሐ 5÷1-25

ቅዳሴ ዘእግዚእነ (ነአኩተከ)

✍️ አምኃ ሥላሴ / መኩሪያ ተስፋዬ 

https://www.tg-me.com/+Vd4rG3DjWHFlDGCo (ቴሌግራም ግሩፕ)

https://m.facebook.com/mekuria.tesfaye.71

https://www.youtube.com/channel/UC8v52_jNY156sxZtplafDtw/about (የዩቱብ አድራሻ)
" ያገኘህን መከራ ሁሉ አመስግነህ ተቀበል፤ ያለ እግዚአብሔር ፈቃድ ምንም ምን የሚደረግ እንደሌለ ዕወቅ " (ሃ.አበ ምዕ 125 ፥ 11 )

እግዚአብሔር ለእኛ ይሻላል ብሎ ከሰጠን በላይ ለእኛ የሚሻል የሚስጠን የለም።

እርሱ ባወቀ የሚጠቅመንን እንጂ የምንሻውን መልስ አይሰጠንም። ይኼ ለእኛ የተሻለ ይሆናል። እኛ የምንሻው ደግሞ ለእኛ አሁን ተጎዳን ካልነው በላይ የሚጎዳን ይሆናል እርሱ ያለው ግን ሁል ጊዜም ለእኛ የተሻለ ነው

ጤንነት ለኃጢአት በሽታ ከሚዳርገን ይልቅ የሥጋ ደዌ ወደ ጽድቅ የሚያመራን ከሆነ ይህ ደዌ የአምላክ ጸጋ ሆኖልናል ማለት ነው።


ሰይጣን የተዋረደው ኢዮብ ደዌውን ስለ ታገሰ ብቻ ሳይሆን ስላላማረረ ነው ።

ደዌ የሚቀለው ተመስገን ስንል ነው። የምናማርር ከሆነ ይህን የሚሻ ሰይጣን ከደዌ በላይ ተስፋ በመቍረጥ እንድንጓዳ ያደርገናል ወደ ማማረር በመድረሳችን ይህንን እርሱ (ሰይጣን) የሚሻው ነውና ዘወትር ፈተና ያደርግብናል እናም ሕመም የሚከብደው ሲያማርሩበት ነውና ደዌው እንዲቀልል ተመስገን እንበል🙏


https://www.tg-me.com/fikarehayimanoti (የቴሌግራም ግሩፕ)

https://m.facebook.com/mekuria.tesfaye.71

https://youtube.com/channel/UC8v52_jNY156sxZtplafDtw (የዩቱብ አድራሻ)
✥✥✥ ደዌና መከራ ✥✥✥

📌 ፪ቆሮ ፲፪ "ስታመም እበረታለሁ "


ለክርስቲያን ደዌና መከራ ብርታቱ ነው።

አምኖ ሳለ ጠግቦ እንደሆነ ደዌው “የሚረዝምበት” ይሆናል።
በክርስትናውም ይበረታ ዘንድ ደዌው “የሚረዝለት” አለ። ስለዚህ ደዌ ስለክፋት "እረዘመበት" ፤ ስለብርታት ደግሞ "እረዘመለት" ተብላ ትነገራለች።

እንደ አባ ዘሚሳኤል ዋጋ ያገኝበት ዘንድ ደዌ ዘኣኮቴት የሚሰጠውም አለ። ይህ ኣባት መላ ዘመኑን በጽኑ ደዌ የኖረ አባት ነበረ ነገር ግን ዘወትር ወደ ጌታችን ፊት እየቀረበ " ጌታ ሆይ ወደ አንተ አብዝቼ እንድቀርብ ያደረገኝን ይህንን ደዌ ስለ ስጠኸኝ አመስግንሃለሁ " ይልም ነበረ። ስለዚህ መከራ አትጥሉ።

📌 " መከራን አትጥሉ "

ስለምንከብርባት ስለ ትሩፋት መከራ መቀበል ክቡድ አይሁንብን። መከራን መጥላት የነፍስ ሕፅፅ ምልክት ነውና። የነፍስ ሕፀፅ መሆኑም በሁለት መልኩ ነው የመጀመሪው እግዚኣብሔር ያድነኛል አለማለት የሃይማኖቱን ሕፀፅ ሲያሳይ በሌላም በኩል የሥጋውን ተድላ መውደዱን ያሳያል።

የእጣን መዓዛ ያለእሳት እንደማይገኝ ክርስቲያንም ያለ መከራ ዕፍረት ምዑዝ የተባለ ክርስቶስ ሊያድርበት አይቻልም :: ቅዱሳን በመከራቸው የክርስቶስ ማደሪያ በመሆናቸው መዓዛ ቅዱሳን ተብሏል።

ጌታችን እርሡ የማይጠቀምበት ቢሆንም ለእኛ ግን ጥቅም ስለሚሆን መከራን ከተቀበለ እኛማ ለራሳችን የምንጠቀምበትን መከራ መቀበልን እንዴት አይገባንም !? መከራ ከክርስቶስ መስቀል መሳተፍ ነው።


📌 መከራ ከክርስቶስ መስቀል የምንሳተፍበት ነው ::

" እኔን መከተል የሚወድ ቢኖር፥ ራሱን ይካድ መስቀሉንም ተሸክሞ ይከተለኝ።" / ማቴ ፲፮፥፳፬ /

✥ በመከራም ከመሰልነው በክብር እንመስልዋለን።

✥ አንድ አባት በሚሞትበት ጊዜ ልጆቹን ሰብስቦ ለበኵር ልጁ አካለ መጠን ያልደረሱ ወንድሞችህ አካለ መጠን ባደረሱ ጊዜ ገንዘባቸውን ስጣቸው ለቁም ነገር አብቃቸው ብሎት ይሞታል ። እነሱም አካለ መጠን ባደረሱ ጊዜ አባታችን ያዘዘልንን ድርሻችንን ስጠን ይሉታል። እርሱም ድርሻችሁን ላቆይላችሁ ብዬ ደክሜኣለሁ ገንዘቤንም አውጥቼአለሁ ስለዚህ እናንተ አስቀድማችሁ ለድካሜም ላወጣሁትም ገንዘቤ ካሳ አግቡልኝ ይላቸዋል። እነርሱም ወጥተው ወርደው ጥፋቱን አግብተው ከብታቸውን ድርሻቸውን እጅ ያደርጋሉ።

✥ እንደዚህም ኹሉ እግዚአብሔር መከራውን በልጁ አበድሯል ዛሬ እስከ ምጽኣት ድረስ የሚነሱ ጻድቃን ሰማዕታት የሚቀበሉት መከራ የዚያን ጥፋት ለማግባት ነው ይኧውም ከክርስቶስ መስቀል የሚሳተፉበትን መከራ መቀበል ነው።

✥ ነገር ግን ሰው በዚህ ዓለም ዕድሜውን ኹሉ የሚቀበለው መከራ ጌታ ለተቀበላት መከራ ዋጋዋ መጠኗ እንዳይደለ ዕውቁ። ፍጡር ዕድሜውን ሙሉ መከራ ሲቀበል ቢኖር ፈጣሪ አንድ ሰዓት ከተቀባላት መከራ አይነጻጸርምና።

✥ እንኳንስ ከክርስቶስን መከራ ሊነጻጸር ይቅርና መንግሥተ ሰማያት ገብቶ አንድ ሰዓት ለሚያገኛት ክብር ዋጋዋ መጠኗ እንዳይደለ ዕወቁ ከአዳም ጀምሮ እስከ ዕለተ ምጽኣት ድረስ የሚነሱ ጻድቃን ሰማዕታት የሚቀበሉት መከራ አንዱ ጻድቅ መንግስተ ሰማይ ገብቶ ለሚያገኛት ክብር ዋጋዋ መጠኗ እንዳይደለ እወቀ :: በሩቅ ብእሲ ደም አትዋጅምና ። ስለዚህ መከራን የምንቀበለው ከክርስቶስ መከራ ለመሳተፍ ነው።

✥ እኛ ከክርስቶስ መስቀል ልናሳተፍ ከፈለግን ግድ በድንጋይ መወገር፣ በእሳት መቃጠል ... ብቻ መጠበቅ የለብንም ብላ ሲልህ እጾማለሁ ፣ ተኛ ሲልህ እጸልያለሁ ፣ እረፍ ሲልህ እሰግዳለሁ ፣ ዘሙት ሲልህ ንጽሕናዬን እጠብቃለሁ፣ አትድንም ሲልህ የማዳኑንን ጊዜ ደጀ እጸናለሁ ብንል መስቀሉን ተሸክመነዋል።

✥ የጌታችንን መስቀል መሽከም ከጠላን ግን ሰይጣን የኃጢኣትን ሸክም ይጭንብናል :: ሠለስቱ ደቂቅ ከእሳቱ ባህር በገቡ ጊዜ እሳቱ አላቃጣላቸውም፣ ነቢዩ ዳንኤልም ከተራቡ አናብስት ቢገባ አልተናጠቁትም ስለዚህ ክርስቲያኖች " መከራን ሲሸሹ ያጠፋቸዋል ሲገቡበት ግን ያጠፉታል። "

📌 ደዌና መከራ ለምን ይቆዩብናል?

✔️ ለማትጋት እና ለማጥራት

ወርቅ እሳት ውስጥ የሚጣለው እንዲጠራ ነው

ከላይ እንደገለጽነው
አምኖ ሳለ ጠግቦ እንደሆነ ደዌው “የሚረዝምበት” ይሆናል።
በክርስትናውም ይበረታ ዘንድ ደዌው “የሚረዝለት” አለ። ስለዚህ ደዌ ስለክፋት "እረዘመበት" ፤ ስለብርታት ደግሞ "እረዘመለት" ተብላ ትነገራለች።

መከራው እንዲቀልልን ወደ እርሱ እንለምናለን። እርሱም ዝም ይለናል። እኛም ያችን ችግር ለማስፈታት ወደ እርሱ ስንመላለስ በዚያው የአባትነቱን ጣዕም ዓውቀን ከእርሱ ጋር ተዋሕደን እንድንቀር ነው፡፡ ይህም ማለት እንደ ውሻ እንዳንሆን ነው። ውሻ ከቤት ይመጣል፡፡ አንድ ቁራጭ ሥጋ ሲጥሉለት ያችን ይዞ ይሮጣል። በኋላ ያቺ ካላለቀች ተመልሶ አይመጣም። እኛም አንድ ጥያቄ ስንጠይቅ ያቺ ዕለቱን ከተመለሰችልን በዚያው ያቺን ይዘን ከቤቱ እንጠፋለን። ምላሹን ካረዘመው ግን ቢሰጠን ይዘን ከቤቱ፣ ባይሰጠንም “አብደርኩ እትገደፍ ውስተ ቤተ እግዚአብሔር እምንበር ውስተ ቤተ ኃጥአን - በኃጥአን ቤት ከምኖር
በእግዚአብሔር ቤት ብጣል” እያልን በዚያው ጸንተን እንድንኖር ነው፡፡

በሉቃስ ወንጌል ጌታ ሁልጊዜ እየሔደች ንጉሡን የምትዘበዝበው ሴት ሁልጊዜ የምትጠይቅ ነፍስ ምሳሌ ናት ይሉናል አባቶቻችን በትርጓሜያቸው የንጉሡ ዝምታ ደግሞ ተላጽቆተ ስኢል እስኪያስደርሰው ድረስ የእግዚአብሔር ዝምታ ነው ብለው ተርጉመዉታል (ሉቃ.፲፰፥፩-፰)፡፡

በሰላም ዘመን ወጣ ገባ እያለ ከእግዚአብሔር እያፈነገጠ እንቢ ያለ ሰው ትንሽ ጉድለት ሲገጥመው ያችን ለማስፈታት ከእግዚአብሔር ደጅ ሲጠና በዚያው በቤቱ ይኖራል። እንኪያስ ወዳጄ ሆይ! ወደህ ፈቅደህ ያለ ችግር ለመመላለስ ዕድልህን ካልተጠቀምክበት በመከራ ገመድነት አምላክህ ይጠራሃልና አትመረር።

መተኛት የእግዚአብሔር ትዕግሥት ስትሆን መቀስቀስ ደግሞ የሰው ጸሎት ነው። ስለዚህ እግዚአብሔር በመከራ ዝም የሚለው እግዚአብሔር በትዕግሥቱ ሰው በጸሎቱ ተዋሕደው እንዲኖሩ ነው። ይህም ፍጹም ቸርነቱ ነው።

ጌታ በመከራ ጊዜ እንደ ተኛ እንዳንቀላፋ ዝም ብሎ በጸሎት ቀስቅሱኝ የሚለን ለጸሎት ዲዳ የሆኑ አንደበቶች ርቱዓት ይሆኑ ዘንድ ነው። ባለመጸለይ ዲዳ የነበሩ ክርስቲያን አንደበቶች የአባታቸው የሥላሴን የእናታቸው የአምላክን እናት በመጥራት በመጸለይ ይፈታ ዘንድ አካላዊ ቃል ክርስቶስ ሳይተኛ ተኝቶ ቀስቅሱኝ” ይላል። “ለበሃማን ኮኖሙ ቃለ - ለዲዳዎች ቃላቸው ነው” እያልን በኪዳን ጸሎታችን የምናመሰግነው ለዚህ ነው፡፡

- እስራኤል የ40 ቀን ጉዞ 40 ዓመት ሆነባቸው

✍️ አምኃ ሥላሴ / መኩሪያ ተስፋዬ 

https://www.tg-me.com/+Vd4rG3DjWHFlDGCo (ቴሌግራም ግሩፕ)

https://m.facebook.com/mekuria.tesfaye.71

https://www.youtube.com/channel/UC8v52_jNY156sxZtplafDtw/about (የዩቱብ አድራሻ)
"አርብ ለፈጠረው አርብ ተሰቀለ። መልኩ ለጠፋ፣ ውበቱ ለረገፈ ዓለም መልክና ውበት ደም ግባት ሆነለት።"

ሊቁ ቅዱስ ዮሐንስ አፈወርቅ
✥✥✥ ልጅም ቢሆን አያውቃትም ✥✥✥

ጥያቄ፡- «....ስለዚያች ቀንና ስለዚያች ሰዓት ግን ከአባት ብቻ በቀር የሰማይ መላእክትም ቢሆኑ ልጅም ቢሆን የሚያውቅ የለም» ሲል ምን ማለቱ ነው? ማቴ.24፡36

መልስ፡- " ልጅም " የሚለው በሁለት ወገን ይፈታል
1– የእግዚኣብሔር የጸጋ ልጅ በሆነው በኣዳም ( ደቂቀ አዳም / በሰው ልጅ )
2– የእዚኣብሔር አብ የባህርይ ልጁ በሆነው በወልድ ይተረጎማል።

1– የእግዚኣብሔር የጸጋ ልጅ በሆነው በአዳም ( ደቂቀ ኣዳም / በሰው ልጅ ) ሲተረጎም፦

👉 ልጅ የተባለው ኦዳም (ደቂቀ አዳም) ነው ሰው የእግዚአብሔር ልጅ ነው (ገላትያ4፦7) ፤ አባት ሲል እግዚአብሔርን ( አብን ወልድን መንፈስ ቅዱስን ነው ) ። ኢየሱስ ክርስቶስን « የዘለዓለም አባት » ተብሏል (ኢሳ 9፥6)

† ስለዚህ ከብቻው ከአብ በቀር (አብ ብቻ ያውቃታል እንጂ) ማለቱ ከፍጡራን ሲለየው ነው እንጂ ከወልድ ከመንፈስ ቅዱስ ሲለየው ኣይደለም።

☞ ለምሳሌ ጌታችን በወንጌል « አንድ ጎልማሳ መጥቶ ፥ " ቸር መምህር ሆይ የዘለዓለም ሕይወትን እወርስ ዘንድ ከበጎ ሥራ ወገን ምን ላድር? " አለው። እርሱም ፥ " ለምን ቸር ትለኛለህ? ከኣንዱ እግዚኣብሔር በቀር ማንም ቸር የለም ፤ ወደ ሕይወት ልትገባ ብትወድድስ ትእዛዛትን ጠብቅ " አለው። …» (የማቴ ወን ምዕ 19፥16–26)

ጌታችን ከአንዱ ከእግዚኣብሔር በቀር ቸር የለም ማለቱ እርሱ እግዚኣብሔር ሳይሆን ቀርቶ አይደለም ስለ እግዚኣብሔርነቱ " ቃልም እግዚኣብሔር ነበር" (ዮሓ ወን ምዕ 1) ተብሎ ተገልጾልናል ነገር ግን ይህ ሰው ቸር መምህር ያለው የክርስቶስን እግዚኣብሔርነት አምኖ ሳይሆን ቸር ብለው ቸር ይለኛል ብሎ ነበር ስለዚህም ጌታችን ከሰው ወገን ፍጹም ቸር የለም በቸርነቱ ስስት የሌለበት አንዱ እግዚኣብሔር ብቻ ነው ቸር ሊባል የሚገባው አንተ ደግሞ እኔ እግዚኣብሔር መሆኔን አላመንክብኝም ለምን ቸር ትለኛለህ ሲለው ነው። በዚህም እራሱን ከፍጡራን ለይቷል እንጂ ከአብ እና ከመንፈስ ቅዱስ (ከእግዚኣብሔርነት) አለየም።

በዚህም ምሳሌ ኣንጻር " ከአባት በስተቀር " ሲል አብን ከእርሱ ከወልድ እና ከመንፈስ ቅዱስ ሲለየው አይደለም ከፍጡራን ሲለየው ነው እንጂ። " ከአባት በስተቀር " ሲል ከእኔም በስተቀር ማለቱ ነው « እኔና ኣብ ኣንድ ነን » (ዮሓ ወን ምዕ 10፥30) እንዲል።

2– የእዚኣብሔር አብ የባህርይ ልጁ በሆነው በወልድ ሲተረጎም፦

👉 ለኣጽድቆተ ትስብእት ( ፍጹም ሰው መሆኑን ለማረጋገጥ ነው።) ወልድ ቅድመ ተዋህዶ የነበረ ኣላዋቂ ሥጋን እንደ ተዋሃደ ለማጠየቅ ነው (ዮሓ ወን 1፥ 14 )። ይህን ማለት ግን ከተዋህዶ በኋላ የክርስቶስ ሥጋ ዓላዋቂ ነው ማለት አይደለም፡፡ሥጋ ከመለኮት ጋር በተዋሕዶ አንድ አካል አንድ ባሕርይ ከመሆኑ በፊት ስላለው መናገራችን ነው፡፡ አኮ ኢያእሚሮ ኅቡኣት ኣላ ከመ የሃብ መካነ ለጥንተ ትስብእቱ ዘኢየኣምር ኅቡዓት እንዲሉ።

ለምሳሌ አልዓዛር መሞቱን ማንም ሳይነግረው አውቆ ለሐዋርያት ነግሯቸዋል። ነገር ግን የተቀበረበትን ቦታ ወዴት ነው ብሎ ጠይቋል መሞቱን ማንም ሳይነግረው ያወቀው እርሱ ሆኖ ሳለ የመቃብሩን ቦታ አሳዩኝ ማለቱ ስለምንድን ነው ቢሉ ጌታችን የተዋሃደው ሥጋ ከተዋህዶ በፊት ኣላዋቂ የነበረውን ሥጋ መሆኑን ለማጠየቅ ነው። ይኸውም አስቀድሞ አባታችን አዳም በበደለ ጊዜ አምላኩን አፍሮ ከበለስ ሥር ተከልሎ ሳለ እግዚኣብሔርም አዳም አዳም ወዴት አለህ ? ብሎ መጠየቁ አዳም ያለበትን ቦታ የማያውቅ ሆኖ አይደለም አላዋቂ የሆነን ሥጋ ተዋህጂ አድንሃለሁ ሲለው ነው እንጂ። (ዮሓ 11/ ዘፍ 3)

👉 አንድም፦ ኢወልድ ባሕቲቱ ዘእንበለ አብ፤ ወልድ ብቻ ያለ አብ አያውቃትም ሲል ነው። ይኸውም ቅድስት ሥላሴ በባህርይ ኩነት አንድ አምላክ ናቸው። በባህርይ ኩነት የአብ ኩነቱ ልብነት ነው ፣ የወልድ ኩነቱ ቃልነት ነው፣ የመንፈስ ቅዱስ ኩነቱ እስትፋስነት ነው። በአብ ልብነት ሁሉን ያውቃሉ ፣ በወልድ ቃልነት ፈቃዳቸውን ይገልጣሉ፣ በመንፈስ ቅዱስ እስትፋስነት ሕያው ሆነው ይኖራሉ። ስለዚህ አንዲት እውቅት ፣ አንዲት ቃል፣ አንዲት ሕይወት አላቸው። በአብ ልብነት ያለው እውቀት ሁሉ በወልድ እና በመንፈስ ቅዱስ ዘንድ ይታወቃል ምክንያቱም አንዲት ልብነት ነውና ያላቸው ስለዚህም ነው ጌታችን ስለርሱ «የአብ የሆነው ሁሉ የእኔ ነው» ያለን፡፡ (ዮሐ.16፡15) ስለመንፈስ ቅዱስም «መንፈስ ቅዱስ የእግዚአብሔርን ጥልቅ(ረቂቅ) ምሥጢሩን ያውቃልና» (1ቆሮ.2፡10) ተብሎ ተገልጻል።

☞ ከወልድ እና ከመንፈስ ቅዱስ የተሰወረ ዕውቀት ለአብ የለውም ፤ ያለ አብ ልብነትም ወልድ እና መንፈስ ቅዱስ ሊያውቁ አይችሉም ምክንየቱም የየራሳቸው ልብነት የላቸውምና በአብ ዘንድ ባለች በልብነት ከዊን ሁሉን ያውቃሉና። በወንጌል « እኔ በአብ እንዳለኹ አብም በእኔ እንዳለ አታምንምን እኔ የምነግራችኹን ቃል ከራሴ አልናገረውም፤ ነገር ግን፥ በእኔ የሚኖረው አብ ርሱ ሥራውን ይሠራል።» (ዮሓ ወን ምዕ 14 ፥10) እንዲል። እኔ የምነግራችሁ ቃል ከራሴ አልናገርም ማለቱ እኔ በራሴ የልብነት ከዊን ኖሮኝ ከራሴ የምነግራችሁ አይደልም በልብነቱ ከዊን ከእኔ ጋር በሚገናዘበው በአብ ልብነት ያወቅሁትን ነው የምነግራችሁ ሲል ነው።

☞ ስለዚህ ከአባት በስተቀር ልጅም ቢሆን ያቺን ዕለት የሚያውቃት የለም ሲል በኣብ ልብነት አውቀናት እንኖራለን እንጂ በእኔ (በወልድ) ቃልነት አትገለፅም ሲል ነው። ለምሳሌ ልብ ቃልና እስትንፋስ ያለው አንድ ሰው በልቡ አስቦት አውቆት ለመናገር ጊዜው ባለመድረሱ ሰዓት እየጠበቀለት ሰውሮ የያዘውን ነገር በቃሉ ሳይናገረው ቢቆይ ቢጠየቅም ዛሬ አልነግረውም ቢል አያውቀውም እንደማይባል ወልድም ያቺን ዕለት ያቺን ሰዓት የምትገለጽበት ጊዜው እስኪደርስ በልቤ አብ ሰውሬ ኣቆያታለሁ እንጂ ዛሬ በቃልነቴ አውጥቼ አልናገራትም ማለቱ ነው እንጂ የማያውቃት ሆኖ አይደለም፡፡

☞ ዕለቱን አለምግለፁም የፍርድ ቀን ሩቅ መሆኑን ካወቁ ነቅተው ተዘጋጅተው በመጠበቅ ፈንታ በኖኅ ዘመን አንደነበሩት ሰብኣ ትካት ( የጥፋት ሰዎች ) ችላ ሊሉ ስለሚችሉ ፤ ጊዜው ቅርብ መሆኑን ካወቁ ደግሞ በጣም ከመፍራታቸው የተነሣ የጌታን ዳግመኛ መምጫ ጊዜ ብቻ በማሰብ የዚህን ዓለም ኃላፊነታቸውን እንዳይዘነጉ ታስቦ ነው፡፡

☞ ከዚህም ባሻገር በሊቃውንተ ቤተክርስቲያን የጌታ ምጽኣቱ ዘመኑ ዘመነ ዮሓንስ ወርኁ ወርኃ መጋቢት ዕለቱ ዕለተ እሁድ ሰዓቱ መንፈቀ ሌሊት ነው ተብሎ ተገልጻል።

ሊቃውንተ ቤተክርስቲያን የዓለም ፍፃሜ መታሰብያን በበዓለ ደብረ ዘይት (በመጋቢት ወር) እና በጳጉሜ ውስጥ እንዲሆን አድርገዋል። ምክንያቱም በዓለ ደብረ ዘይት ጌታ ስለዓለም ፍፃሜ ለሐዋርያት ያስተማረበት ቀን ስለሆነ ፤ ጳጉሜ የዘመን ፍፃሜ ስለሆነ በሁለቱ ጊዜያት የዓለም ፍፃሜ ይሆናል ተብሎ በቤተክርስቲያናችን ይጠበቃል።

በዘመነ ዮሓንስ መባሉ የወንጌላውያን መጨረሻ ቅዱስ ዮሐንስ ነው።" ጥንቱሰ ለወንጌላውያን ማቴዎስ ወፍፃሜሁ ዮሓንስ" እንዲል። ዓለም የተፈጠረው እንዲሁም ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ የተፀነሰው በዘመነ ዮሓንስ በመሆኑን ነው። በሌሊት መባሉም ጌታችን ለሓዋርያት የምጽኣቱን ነገር ሲነግራቸው « ያን ግን ዕወቁ፤ ባለቤት ከሌሊቱ በየትኛው ክፍል ሌባ እንዲመጣ ቢያውቅ ኖሮ፥ በነቃ ቤቱም ሊቈፈር ባልተወም ነበር። ስለዚህ፥ እናንተ ደግሞ ተዘጋጅታችኹ ኑሩ፥ የሰው ልጅ በማታስቡበት ሰዓት ይመጣልና። » (ማቴ 24 ፥ 43–44) ያለውን ቃል
መሠረት በማድረግ ነው።

☞ ዕለቲቱን ማንም አያውቃትም ተብላል አይደለምን ቢሉ ብዙ ዘመነ ዮሓንስ ብዙ ወርኃ መጋቢት ብዙ ዕለተ እሁድ ብዙ መንፈቀ ሌሊት አሉና ይህ አይታወቅም ሲል ነው። ጌታችን በሚመጣበት ጊዜ በቀኝ ከሚቆሙት ጋር ለመደመር ያብቃን።

✍️ አምኃ ሥላሴ / መኩሪያ ተስፋዬ 


https://www.tg-me.com/+Vd4rG3DjWHFlDGCo (ቴሌግራም ግሩፕ)

https://m.facebook.com/mekuria.tesfaye.71

https://www.youtube.com/channel/UC8v52_jNY156sxZtplafDtw/about (የዩቱብ አድራሻ)
✥✥✥ በዐለ ደብረዘይት ✥✥✥

ትርጉሙ፦ ደበረ ዘይት ትርጉሙ የወራ መብቀያ፣ በወይራ ደን የተሸፈነ ተራራ ማለት ነው። ወይም «ደብር» ማለት «ተራራ» ማለት ሲሆን «ዘይት» ማለት ደግሞ «ወይራ» ማለት ነው። በተገናኝ «ደብረ ዘይት» ማለት የወይራ ዛፍ የሞላበት፣ የበዛበት፣ የወይራ ተራራ ማለት ይሆናል።

- ከኢየሩሳሌም በስተምሥራቅ የሚገኝ ቦታ የሚገኝ ተራራ ሲሆን በመካከል የቄድሮን ሸለቆ ብቻ ነው ያለው። ከግርጌው ጌቴ ሴማኒ የተባለው የአትክልት ስፍራ ይገኛል። የጸሎተ ሐሙስ ማታ ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ የተያዘበትና በኋላም የእመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ቅዱስ ሥጋዋ ያረፈበት ወይም የድንግል መካነ መቃብር በዚህ
ተራራ ግርጌ ይገኛል። ቤተ ፋጌ እና ቢታንያ በኮረብታው ጫፍ እና በምስራቅ ዳገታ ላይ ይገኛሉ።

- ይህ ተራራ በመፅሐፍ ቅዱስ የሚገኙ ብዙ ድርጊቶች የተደረጉበት ቦታ ነው። ጌታችን ስለ ቤተ መቅደሱ መፍረስ፣ ስለ ዓለም ፍጻሜና ስለ ዳግም ምጽአት በዚህ ተራራ ላይ በትንቢት መልክ ተናገረ (ማቴ.24፥3)። በዚሁ ተራራ ላይ ወደ ሰማይ ዐረገ (ሉቃ.24፥50)። በዚሁ ተራራ ላይ ቀን በከታማና በገጠር ሲያስተምር ውሎ ሌሊት የሚያድርበት የኤሌዎን ዋሻ ይገኛል።
በኋለኛው ምጽአቱ በዚሁ ቦታ እንደሚገለጥ ትንቢትተነግሯል።(ዘካ. 14፥3-5)።

- ስያሜው፦ የዓቢይ ጾም እኩሌታ ላይ ያለው ሰንበት በዚህ ተራራ ተጠርቷል። ይህንን ዕለት የቤተ ክርስቲያናችን ሊቅ ቅዱስ ያሬድ የዳግም ምጽአት አድርጎ መዝሙሩን ጽፏል። በዚህ ተራራ ላይ «እርሱም በደብረ ዘይት ተቀምጦ ሳለ፥ ደቀ መዛሙርቱ ለብቻቸው ወደ እርሱ ቀርበው። ንገረን፥ ይህ መቼ ይሆናል? የመምጣትህና የዓለም መጨረሻ ምልክቱስ ምንድር ነው? አሉት» (ማቴ.24፥3)። ተብሎ እንደተጻፈው
ለደቀ መዛሙርቱ የደግም ምጻቱን፣ የዓለምን ፈጻሜ፣ የትንሣኤ ሙታንን፣ ትምህርት በሰፊው ስላስተማረ በዓሉ በተራራው ስም ተሰይሟል።

አመጣጡስ እንዴት ነው?

- ጌታ ይህንን ዓለም ለማሳለፍ ለሁሉም እንደ ሥራው ለመክፈል በግርማ መለኮቱ በክበበ ትስብዕቱ ይመጣል፡፡ ጊዜው ዘመነ ዮሐንስ ወርኃ መጋቢት ዕለተ እሑድ መንፈቀ ሌሊት እንደሆነ ሊቃውንት ተናግረዋል፡፡
ምነው ‹‹ የሚያውቀው የለም ይል የለምን ቢሉ እውነት ነው የሚያውቀው የለም ብዙ የዮሓንስ ዘመን ብዙ የመጋቢት ወር ብዙ የእሑድ ዕለት የበዙ ሌሊቶች አሉና ለይቶ የሚያውቅ የለም ለማለት ነው፡፡

-> ሞት ለማንም ኣይቀርምና ሁሉም ይሞታል፡፡ ዘፍ 3፡19 በዕለተ ምጽኣትም ቅዱስ ገብርኤል ስምንቱን ነፋሳተ መዓት ከየመዛግብታቸው ያወጣቸዋል፡፡ ዛፍን ነቅለው ድንጊያውን ፈንቅለው ምድርን እንደብራና ይዳምጧታል፡፡ ቅዱስ ሚካኤል ነጋሪቱን ይመታል ፩ኛመቃብ ፱፥፰ ነጋሪት የተባለው በቁሙ ነጋሪት የሚመታ ሆኖ ሳይሆን አዋጁን የምትክ ንቃ የሚል አዋጅ የሚናገር ይታወጃልና ነጋሪት ይመታል አለ

. ስለዚህ ቅዱስ እግዚኣብሔር ቅዱስ ዘያነቅሖሙ ለሙታን ሲል በዱር በገደል በባህር በየብስ በመቃብር ውስጥ ያሉት በአውሬ ሆድ ውስጥ ያሉ ሁሉ ይሰበሰባሉ፡፡
. በሁለተኛው ነጋሪት ሲመታ አጥንትና ሥጋ አንድ ሆነው ፍጹም እንደ ዕለት በድን ይሆናሉ፡፡
. ሦስተኛው ነጋሪቱን መትቶ /ቅዱስ እግዚኣብሔር ቅዱስ ኃያል ቅዱስ ህያው ዘኢይመውት / ንቃሕ መዋቲ ዘትነውም ባለ ጊዜ መቃብር ክፈቱልኝ መግነዝ ፍቱልኝ ሳይል ደጉ ደግነቱን ክፉውም ክፋቱን ይዞ ይነሳል፡፡

- ወንዱ የ30 ዓመት ሴቲቱ የ15 ዓመት ሆነው ጻድቃን ብርሃን ለብሰው ብርሃን ተጎናጽፈው ከፀሐይ 7 እጅ አብርተው ማቴ 13፡43
ኃጥአን ጨለማ ለብሰው ፍጹም ዲያብሎስን መስለው ይነሳሉ፡፡ ጻድቃን ስለሠሩት መልካም ሥራ ኑ የኣባቴ ብሩካን ብሎ መንግሥተ ሰማያትን ያወርሳቸዋል፡፡ ኃጥኣንን ስለክፋ ሥራቸው /ከኔ ሂዱ/ ብሎ ገሃነም ይሰዳቸዋል፡፡
ጻድቃን ደስ ይላቸዋል ኃጥአን ግን ያዝናሉ ዋይ ዋይ እያሉ ደረት ይደቃሉ እንባቸውን ያፈሳሉ፡፡ የማይጠቅም ልቅሶ የማይረባ ኃዘን ነው ሰቅለው የገደሉትም አይሁድ ክብሩን 0ይተው ላይጠቀሙ ይጸጸታሉ፡፡

- በዳግም ምጽአቱ ጊዜ ከቅዱሳኑና ከሰማዕታቱ ጋር ለመቆም ያብቃን፡፡🤲

-> መዝሙር ዘደብረ ዘይት እንዘ ይነብር እግዚእነ ወስተ ደብረ ዘይት ይባላል

-> ምንባብ ዘቅዳሴ
- 1ተሰሎ 4÷13-ፍም::
- 2ጴጥ 3÷7-15::
- ግሐዋ 24÷1-22

-> ምስባክ
" እግዚአብሔርሰ ገሀደ ይመፅእ፣ ወአምላክነሂ ኢያረምም እሳት ይነድድ ቅድሜህ" መዝ 49÷2

-> ወንጌል፦ ማቴ፡ 24÷1-36

-> ቅዳሴ አትናቴዎስ

✍️ አምኃ ሥላሴ / መኩሪያ ተስፋዬ 


https://www.tg-me.com/+Vd4rG3DjWHFlDGCo (ቴሌግራም ግሩፕ)

https://m.facebook.com/mekuria.tesfaye.71

https://www.youtube.com/channel/UC8v52_jNY156sxZtplafDtw/about (የዩቱብ አድራሻ)
ልጅሽ በደሙ የዋጀኝ እኔን እንድጎዳ አትጣይኝ
ልጅሽንም እንዲህ በይ። ይህንን ጎስቋላ ባሪያ በክቡር ደምህ የገዛኸውን ስለ በደሉ ስለ ጉስቁልናው አትናቀው ገንዘቡን በወርቁ የገዛውን ለመጥላት የሚችል የለምና ።
ልጄ ሆይ በደምህ የገዛኸውን ኃጢአተኛውን ባሪያህን እንግዲህ እንዴት ትንቀዋለህ አይደለም ። ይህንን ፍዳ አታድርግ ከባሪያህም ጋራ ወደ ክርክር አትግባ ሕያዊት ነፍስ ያለችው ሁሉ ባንተ ፊት እውነተኛ አይደለምና ።
ልጄ ሆይ የኃጢአቱን ቁጥር አታስብ ። እንደበደሉም አታድርግበት። ስለ ኃጢአቱም አትበቀለው ። በሰውነቱም ቢበድል በገቢርም በሐልዮም ቢሆን ስለ ፍዳ እኔ ጸሎትን ማማለድን እከፍላለሁ። ይቅርታህ ያባትህም ቸርነት የመንፈስ ቅዱስም ምሕረት በዘመኑ ሁሉ ባርያህን ይጎብኘው ይርዳው ለዘለዓለም በእውነት ያለ ሐሰት አሜን ።
( አባ ጊዮርጊስ ዘጋስጫ የዐርብ አርጋኖን )
#ገዳይ_አሸናፊ_የማይሆንበት_ጦርነት

-> ቃየን ወንድሙን አቤልን ቢገድለውም አቤል ተሸናፊ ቃየን አሸናፊ አልሆኑበትም ይልቁንም ወንድሙን ገዳይ ቃየል የተረፈው " የሚያገኘኝ ሁሉ ይገድለኛል ብሎ በምድር ላይ ተቅበዝባዥ ሆኖ መኖር ነው " ይህም የሆነው የተገዳይ የአቤል ደም (ነፍስ) በአምላክ ፊት የከሰሰችው በመሆንዋ ነው።

-> የገዳይ ትርፉ ጭንቀት ነው ይልቁንም ወንድም ወንድሙን ሲገድለው ከሚሞተው ይልቅ ገዳዩ እጅጉን ተጎጂ ነው ለምን ቢሉ ወንድሙ በርሱ እጅ እንደወደቀ ርሱ በእግዚኣብሔር እጅ ይወድቃልና " በቀል የእኔ ነው ፥ እኔ ብድራትን እመልሳለኹ ያለውን እናውቃለንና ደግሞም ፦ጌታ በሕዝቡ ይፈዳል፤ በሕያው እግዚኣብሔር እጅ መውደቅ የሚያስፈራ ነው። (ዕብ ፲፥፴-፴፩፡፡) አዎን በእግዚኣብሔር እጅ መውደቅ እጅግ ያሰፈራል !!!

-> ኢትዮዽያ ሃገራችን የገጠማት ይኸው ነው ልጆችዋ እንደተጣሉባት እንደ ርብቃ ማህፀን ሆናለች። እንግዲህ ተስፋዋ ሰላምዋም እርሱ እግዚኣብሔር ነውና " አምላከ ሰላም ተራድኣነ " እያልን እንማፀነው።

https://www.tg-me.com/+Vd4rG3DjWHFlDGCo (ቴሌግራም ግሩፕ)

https://m.facebook.com/mekuria.tesfaye.71

https://www.youtube.com/channel/UC8v52_jNY156sxZtplafDtw/about (የዩቱብ አድራሻ)
✥ገብር ኄር✥
"መንግሥተ ሰማያት ነጋዴ ናት "

-> መንግሥት ሰማያት ነጋዴ ናት ትርፍን ትፈልጋለች ስለዚህ በመጽሐፍ መንግሥት ሰማያት ብላቴኖቹን ጠርቶ ወጥተው ወርደው ያተርፉበት ዘንድ ገንዘቡን የሰጣቸውን ነጋዴ ትመስላለችና ይላል። (ማቴ ፳፭፥፲፭)

-> ሹመትም ውርደቱም ፣ መጽደቅ መኮነንም በዋጋ (በጸጋ) ሳይሆን በትርፍ ነው። 5 እና 2 መክሊት የተሰጣቸው አገልጋዮች የተሾሙት በትርፋቸው እንጂ ቀድሞ የተሰጣቸውን መክሊት በማቆየታቸው አይደለም ፥ 1 መክሊት የተሰጠውም ባሪያ የተኮነነው የተሰጠውን መክሊት በማጥፋቱ አይደለም ባለማትረፉ እንጂ መክሊቱንስ አስቀምጦ ጌታው በመጣ ጊዜ መልሶለት ነበር በተሰጠው ባለማትረፉ ግን ቀድሞ የተሰጠውን መክሊት ሳያጠፋ ጠብቆ በመገኘቱ ብቻ ከመኮነን አላዳነውም። ስለዚህ ጽድቅና ኵነኔ በትርፍ መሆኑን ተረዳን።
በማቴ 25 ላይም በምሳሌው የተገለጸው ይህንን የሚያስረዳ ነው

ባዕል ነጋዴ ብሎ ጌታን (መንግሥተ ሰማያት) ፣ አግብርት ብሎ መምሕራንን ካህናትን ማምጣት ነው።

-> ባለ ፭. ፪ትም የተባሉት ፍጹም ትምህርት ተምረው መክረው አስተምረው ራሳቸውን አስመስለው ያወጡ መምህራን ናቸው:: ጴጥሮስ ቀሌምንጦስን፣ ጳውሎስ ጢሞቴዎስን እንዳወጡ፡፡

- እነዚህ መምህራን በትምህርት የሚወልዱ በመሆናቸው ብዙ ተባዙ ያለውን ቃል የፈጸሙ ናቸው

-> ባለ ፩ የተባለ ተምሮ ሳያስተምር የቀረ ነው:: ዐላውያን እሳት ስለት አሳይተው ቢያስክዱኝ፣ መናፍቃን ተከራክረው ምላሽ ቢያሳጡኝ ብሎ፤ ሃይማኖቱን በልቡ የያዘ ነው::

- ይህን ባሪያ የመሰሉ በትምህርት የማይወልዱ የጋን መብራቶች ሜልኮላውን ናቸው። ይህም በአባ መልክአ ክርስቶስ ታውቋል ። ፍጹም ትምርት ተምረው ሳለ ሳያስተምሩ ቀርተዋል በተባሕትዎ መላ ዘመናቸውን ፈጽመውታል ። በሚሞቱበት ጊዜ መልአክ ገሠጻቸው ። ቀለሙ አካል እየገዛ ሲወጣ ታይቷል ።

-> ጸጋ ስጦታ ነው መመስገኛም መወቀሻም የሚሆነው ግን በተሰጠ ጸጋ በሚሠሩት ሥራ እና ባለ መሥራት ነው። የነጋዴ ጥቅሙ በትርፍ እንደሆነ ሰው መሾም መሻሩ ፥ መጽደቅ መኮነኑ በተሰጠው ጸጋ ሌላው ምዕመናን ትርፉ በማድረጉ ነው።
- በምሳሌውም " ላለው ይጨመርለታል " ያለው ጸጋ ላለው ጸጋ ይጨመርለታል ማለቱ ሳይሆን በተሰጠው ጸጋ ትርፍ ያለው ሰው ሌላ ያተርፍ ዘንድ ጸጋ ይጨመርለታል ማለት ነው

" ለሌለው ግን ያለውን ይወሰድባታል " ማለቱም ትርፍ ለሌለው ግን እንኳንስ ሌላ ጸጋ ሊሰጠው ቀርቶ ቀድሞ የተሰጠው ጸጋ ይወስድበታል ማለቱ ነው።
- ስለዚህ መንግሥተ ሰማያት ነጋዴ ናት ያተረፉ የሚገቡበት የትሩፋን ሀገር ናት።

-> መዝሙር ዘገብርኄር ፦ መኑ ውእቱ ገብርኄር ወምዕመን

-> ምንባብ ዘቅዳሴ
- 2ጢሞ 2÷1-16
- 1ጴጥ 5-1-12
- ግ.ሐዋ 1፥6-9

-> ምስባክ ፦ " ከመ እንግር ፈቃደከ መከርኩ አምላኪየ ወሕግከኒ በማዕከለ ከርሥየ ዜኖኩ ጽድቀከ በማኅበር 0ቢይ " መዝ 39፥8

-> ወንጌል :- ማቴ 25÷14-31

-> ቅዳሴ :- ዘባስልዮስ

✍️ አምኃ ሥላሴ / መኩሪያ ተስፋዬ 

https://www.tg-me.com/+Vd4rG3DjWHFlDGCo (ቴሌግራም ግሩፕ)

https://m.facebook.com/mekuria.tesfaye.71

https://www.youtube.com/channel/UC8v52_jNY156sxZtplafDtw/about (የዩቱብ አድራሻ)
2024/04/26 02:38:00
Back to Top
HTML Embed Code: