#በመቃብር_አደረ

"ዳግመኛም ይህ ሥጋ ከመለኮቱ ሳይለይ በመቃብር አደረ ነፍሱም ከመለኮት ሳትለይ በገሀነም ተግዘው ለነበሩ ነፍሳት ድኅነትን ታበስር ዘንድ፤ ነፃም ታደርጋቸው ዘንድ ወደ ሲኦል ወረደች።"

ሃይማኖተ አበው ዘአትናቴዎስ
"ድንግል ሆይ በኃጢአት ፍትወት የተፀነስሽ አይደለም፤ በሕግ በሆነ ሩካቤ ከሐና ከኢያቄም ተወለድሽ እንጂ።"
አባ ሕርያቆስ
እንኳን ለእመቤታችን ለቅድስት ድንግል ማርያም በዓለ ልደት አደረሰን 🙏🙏🙏
"ሰይጣንም የአንቺን ምስጋና ወሬ ሲሰማ በብስጭት ጥርሱን ያፏጫል፤ የምስጋናሽ ወሬ በእርሱ ዘንድ መራጃ ነውና እራሱን ይቆርጠዋል፡፡ ከስምሽ አጠራር የተነሣ መብረቅ በኃይል ሲጮህ እንደ ሰማ ሁሉ ይደነግጣል፡፡ አንቺ ከተወለድሽ ጀምሮ ፈጽሞ ዕረፍት አላገኘም፡፡ በአንቺ ታመመ በልጅሽም ተጨነቀ በአንድ ልጅሽ መስቀል ሥቃይ አገኘው፡፡ ከፍጡራን ወገኖች ሁሉ ይልቅ ሰይጣል አንቺን ይጠላል፡፡"

#አባ_ጊዮርጊስ_ዘጋስጫ
ብሒላተ አበው ወእመት ዘኦርቶዶክስ ተዋሕዶ
Photo
[•• አምስቱ ትንሣኤዎች••]
      
‹‹...በፊተኛው ትንሣኤ ዕድል ያለው ብፁዕና ቅዱስ ነው ሁለተኛው ሞት በእርሱ ላይ ሥልጣን የለውም፡፡›› ራእ ፳ ፥ ፮

ኦርቶዶክሳውያን ሊቃውንት «ትንሣኤን» በየመልኩ፣ በየዐይነቱ ሲያመሠጥሩት በአምስት ዓይነት ትርጉም ያስቀምጡታል፡፡

ይኸውም ትንሣኤ ኅሊና፣ ትንሣኤ ልቡና፣ ትንሣኤ ሙታን፣ ትንሣኤ ክርስቶስና ትንሣኤ ዘጉባኤ በሚል በአምስት መንገድ ይከፈላል።

፩ኛ. ትንሣኤ ኅሊና ነው
ይህ ትንሣኤ ኅሊና ተዘክሮተ እግዚአብሔር (እግዚአብሔርን ማሰብ) ማለት ነው። ሙሴ በኦሪቱ ‹‹እመኒ እንዘ ተሐውር ወእመኒ እንዘ ትትነሣእ ኢትርሣእ ተዘክሮተ እግዚአብሔር፡፡ ስትሄድም ስትነሣም እግዚአብሔርን ማሰብ አትርሣ›› ብሎ ሊቀ ነቢያት ሙሴ እንደተናገረው።

፪ኛ. ትንሣኤ ልቡና ነው፤
ትንሣኤ ልቡና ደግሞ ቃለ እግዚአብሔርን በመስማትና በንስሐ እየታደሱ በሕይወት መኖር ማለት ነው:: ይኸውም ሰው ሁለት ጊዜ ይሞታል፤ ሁለት ጊዜ ይነሣል፤

የሰው ልጅ የመጀመሪያው ሞቱ ኀጢአት መሥራቱ ከእግዚአብሔር መለየቱ ነው፤ ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ በሥጋ ፍትወት በምድራዊ ቅንጦት የሚቀማጠሉትን ሲናገር ‹‹ቅምጥሊቱ ግን በሕይወቷ ሳለ የሞተች ናት›› ፩ኛ ጢሞ ፭ ÷፲ ፯ ሲል በኀጢአት መኖር ትልቁ ሞት እንደኾነ ነግሮናል፣

ሁለተኛው በሥጋ መሞቱ ነው:: ስለዚህ ሰው ሁለት ጊዜ እንደሚሞት ሁለት ጊዜ ይነሣል፤

የሰው ልጅ የመጀመሪያ ትንሣኤው እንዴትና ምን እንደሆነ ቅዱስ ዮሐንስ በራእዩ እንዲህ ሲል ነግሮናል፤ ‹‹ይህ የፊተኛው ትንሣኤ ነው፤ በፊተኛው ትንሣኤ ዕድል ያለው ብፁዕና ቅዱስ ነው
ሁለተኛው ሞት በእርሱ ላይ ሥልጣን የለውም፡፡›› ራእ ፳ ፥ ፮  በማለት ንስሐ ገብቶ ከእግዚአብሔር ታርቆ ትንሣኤ ልቡናን ገንዘብ ያደረገ ሰው ሞተ ሥጋንና ሞተ ነፍስ ድል ነሥቶ እንደሚኖር ነግሮናል፡፡ 

ለትንሣኤ ልቡና ትልቅ ምክር የሚሆነን በሉቃስ ወንጌል የተመዘገበው ታሪክ ነው፤  ‹‹ይህ ልጄ ሞቶ ነበረና ደግሞም ሕያው ሆኗል፤ ጠፍቶም ነበር ተገኝቷል›› በማለት በኀጢአት መኖር እንደ መሞት ከኀጢአት መመለስ እንደ ትንሣኤ መቆጠሩን አስረድቶናል። ሉቃ ፲፭ ፥ ፳፬ ማንኛውም ሰው ከቤተ ክርስቲያን ከመንፈሳዊ ሕይወት ከወጣ እንደ ሞተ ነው የሚቆጠረው፡፡

፫ኛ. ትንሣኤ ሙታን ነው
ይህ ደግሞ ለጊዜው የሙታን በሥጋ (በተአምራት) መነሣት ሲሆን፤ ነገር ግን ድጋሚ ሞት ይከተለዋል:: ይኸውም በብሉይ ኪዳን ነቢዩ ኤልያስ አንድ ሙት፣ ነቢዩ ኤልሳዕ ሁለት ሙት አስነሥተዋል፤ በሐዲስ ኪዳን ጌታችን የዐራት ቀን ሬሳ አልአዛርን፣ የዕለት ሬሳ ወልደ መበለትን፣ ወለተ ኢያኤሮስን ከሞት አስነሥቷል፤ ይህ ‹‹ትንሣኤ ሙታን›› ይባላል፡፡

፬ኛ. ትንሣኤ ክርስቶስ ነው
ትንሣኤ ክርስቶስ እንደሚታወቀው ጌታችን መድኀኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በገዛ ሥልጣኑ ሞትን ድል አድርጎ መነሣቱን የሚገልጥ ነው:: ይህ ትንሣኤ የትንሣኤው ሁሉ በኵር ተብሎ ይጠራል᎓᎓ ትንሣኤው ከፍጡራን ትንሣኤ የተለየና ብቸኛ ነው:: 

፭ኛ. ትንሣኤ ዘጉባኤ ነው
ትንሣኤ ዘጉባኤ ከዓለም ኅልፈት በኋላ ሰው ዅሉ እንደየሥራው ለጽድቅና ለኩነኔ በአንድነት የሚነሣው የዘለዓለም ትንሣኤ ነው።

በሕብረት፣ በነገድ፣ በጉባኤ ለዓለም ሕዝብ ሁሉ የሚደረግ ትንሣኤ በመሆኑ ትንሣኤ ዘጉባኤ ተብሏል። ጌታ በወንጌሉ ስለትነሣኤ ዘጉባኤ ሲናገር «በመቃብር ያሉት ሁሉ ድምፁን
የሚሰሙበት ሰዓት ይመጣል፤ መልካምም ያደረጉ ለሕይወት ትንሣኤ፤ ክፉም ያደረጉ ለፍርድ ትንሣኤ ይወጣሉና በዚህ አታድንቁ።» ዮሐ ፭ ፥ ፳፱ ሲል በትንሣኤ ዘጉባኤ ከሚደረጉ ተአምራት አንጻር ዛሬ የሚደረጉ ተአምራት ምንም እንዳልሆኑ አስተምሯል። ትንሣኤ ክርስቶስ ለትንሣኤ ሙታን ምስክር ለትንሣኤ ዘጉባኤ በኵር  ነው
   ©መ/ር ሚኪያስ ዳንኤል
ክርስቶስ ተነሥቷል(Christ Risen) በሚለው ቃል ውስጥ ያለው መንፈሳዊ ኀይል።

በአባ ዮሐንስ ገባሬ መንክራት (St. Jonh Maximivotch) የተደረገው ተአምር።

አባ ዮሐንስ ገባሬ መንክራት በአንድ ወቅት የብርሃን ሳምንት ተብሎ በሚታወቅበት ሳምንት አንድ የታመመ ኦርቶዶክዊ ምዕመንን ለመጠየቅ ጉዞውን ወደ አንድ የአይሁዳውያን ሆስፒታል ያደርጋሉ።

አባ ዮሐንስ በሆስፒታሉ በአንደኛው ዋርድ ፊትለፊት ሲያልፍ ድንገት ቆመና በመጋረጃ በተሸፈነው ክፍል ውስጥ አንዲት አይሁዳዊት አሮጊት ሕይወቷ አልፏል በመባሉ ሸፋፍነዋት አልጋ ላይ እንዳስተኟት ይረዳል።

አባ ዮሐንስ ገባሬ መንክራት ድንገት ከተጋረደው ክፍል ፊትለፊት ቆመና ቅዱስ መስቀሉ አውጥቶ ድምጹ ከፍ አድርጎ ጮኸና "ክርስቶስ ተነሥቷል" እያለ በመስቀል ምልክት እያማተበ ተናገረ፣ ድንገት ይኸንን በሚያደርግበት ወቅት ሞተች የተባለችዋ እናት አእምሮዋ ተመለሰላትና ቃል አውጥታ ውሃ ስጡኝ ብላ ጠየቀች።

አባ ዮሐንስም አንዷን ነርስ ጠራት እንዲህ አላት ታማሚዋ ውሃ እየፈለገች ነው ብሎ ሲነግራት ይኸንን የሰሙ የሆስፒታሉ ሠራተኞችም አስቀድማ አርፋለች ተብላ የነበረችው ታማሚዋ ባሳየችው አስገራሚ ለውጥ በጣም ተደነቁ ከዚያ በኋላ ታማሚዋም በተደረገላት አስደናቂ ተአምር ተሽሏት አገግማ ከሆስፒታሉ ወጥታ ወደ ቤቷ ሔደች።

አባ ዮሐንስም በክርስቶስ የትንሣኤው ኃይል በማያምኑት መካከል አስደናቂውን ተአምር አደረጉ።

አቤቱ ሆይ የትንሣኤህ ኃይል ይገለጥ ሰይጣን ከነ ሠራዊቱ ይሸነፍ፣ ሞትም ከነ መውጊያው ይወገድ፣ ሲኦልም ከነ ድል መንሣቷ ትሻር፣ ኃጢአት እና አለማመን ከእኛ ይራ፣ ሕይወታችን የተቀደሰች ትሁን ዙሪያችን በትንሣኤው ኃይል በትንሣኤው ብርሃን የታጠረ ይሁን።

ክርስቶስ ተነሥቷል
በእውነት እርሱ ተነሥቷል።
በአንዳች ነገር መጠን ባለፈ ሁኔታ እየተጨነቅንና እየተበሳጨን ከሆነ ፈቃድህ ይሁን ብለን ብንጸልይም እንደ ጌታ ፈቃድ ያለመኖራችንና ለእግዚአብሔር ፈቃድ ሙሉ በሙሉ እጅ እንዳልሰጠን ማሳያ ነው።።
እንደ እግዚአብሔር ፈቃድ የሚኖር ሰው ስለ ምንም ነገር አይጨነቅም።ፈቃድህ ይሁን ብሎ እራሱን እና ፍላጎቱን ለእግዚአብሔር አሳልፎ ስለሚሰጥ የሚፈልገውን ባያገኝ እንኳን በትዕግስት ጸንቶ ጌታን ያመሰግናል።
ለእግዚአብሔር ፈቃድ የተገዛች የክርስቲያን ነፍስ በምንም ነገር አትታወክም አትፈራም አትጨነቅምም።ትናንትን ያሻገራት ዛሬን የሚጠብቃት ነገን ከበረከት ጋር የሚያሳያት ጌታ እንዳላት ታምናለችና።አሜን

~ ቅዱስ ሰሎዎስ ዘአቶናዊ
በእውነት የተመሰገኑት ተአምራትን ማድረግና ቅዱሳን መላእክትን ማየት የቻሉት ብቻ ሰዎች ሳይሆኑ የተመሰገኑት የራሳቸውን በደል ማየት የቻሉት ሰዎችም ናቸው።

ቅዱስ አትናቴዎስ
ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ "ክርስቶስ ካልነሣማ እምነታችን ከንቱ ናት" 1 ቆሮ.15፦17) እንዳለው የክርስቶስ ትንሣኤ እርሱ የሚጠበቀው መሲህና የእግዚአብሔር ልጅ ለመኾኑ ፍጹም ማረጋገጫ ነው። ክርስቶስ ከሞት በመነሣቱ ምክንያት ነፍሳችን የኢመዋቲነት(የሕያውነት) እና የዘለዓለማዊነት ተስፋን ትቀበላለችና።
ጎርጎርዮስ ፓላማስ(St. Gregory Palamas)
"ከዓወሎ ነፋስ የተነሣ ምዕመናንን የምታሻግር የመድኃኒት ድልድይ, የድኅነት መርክብ ሆይ ክኃጢአት ማዕበል ሞገድ አሻግሪኝ, መርክብ ሰውነቴን እንዳያነዋውፀው። "
አባ ጊዮርጊስ ዘጋዝጫ
ብሒላተ አበው ወእመት ዘኦርቶዶክስ ተዋሕዶ
Photo
መንፈሳዊ ሕይወትን

ገና ስትጀምረው ለፍጹምነት ጥቂት የቀረህ ያህል ይሰማሃል። አንተ ጋር ያለው ደስታ እና ሰላም ሌሎች ጋር የሌለ ይመስልሃል። በዚህች ሁከት በሞላባት ዓለም አንተ ብቻ ክርስቶስን እንዳገኘኸው ታስባለህ። የቀረው ሕዝበ አዳም እንዲሁ በከንቱ ሲርመሰመስ የሚውል ባካና ሆኖ ይታይሃል። ታዝንለታለህ፣ አይይይ ይህ ኃጢአተኛ ሕዝብ ምን ይሻለዋል? ትላለህ።

የእውነተኛ መንፈሳዊ እድገት መገለጫ ግን ይህ አይደለም። ሰው ወደ እግዚአብሔር እየቀረበ ሲመጣ ከሌላው ሰው ይልቅ የራሱ ጉድለት ይታየዋል። መንፈሳዊነት የሚገልጥልህ ሰዎችን ተመልክተህ የምትፈርድበትን ውጫዊ ዓይንህን ሳይሆን ራስህን አይተህ የምትወቅስበት የውስጥ ዓይንህን ነው። መንፈሳዊ ሕይወትህ ሲጎመራ "አይ ሰው" ሳይሆን "አይ እኔ!" ያሰኝሃል። "ሰው የበለጠ ወደ እግዚአብሔር ሲቀርብ ይበልጥ ኃጢአተኛ መሆኑ እየታየው ይመጣል። ነቢዩ ኢሳይያስ እግዚአብሔርን ካየ በኋላ ከንፈሮቼ የረከሱብኝና የጠፋሁ ሰው ነኝ እንዳለ።"

ከብቃት ደርሰህ መላእክት ሲወጡና ሲወርዱ ቢታዩህ እንኳን ሁሉ እንዳንተ ስለሚመስልህ እንደ ዮሐንስ ሐጺር "ሚካኤል ይበልጣል ወይስ ገብርኤል?" እያልህ ከአጠገብህ የቆመውን ትጠይቃለህ እንጂ "አይይ አንተ እንኳን ገና አልበቃህም። ብዙ ይቀርሃል" ብለህ ወዳጅህን አታናንቅም። ይልቅ "ለእኔ ብቻ ገልጦ ለሌላው እንዲሰውር የሚያደርገው ምንም ቁም ነገር የለኝም" በማለት ከወንድምህ የተሻልህ እንዳልሆንክ በፍጹም ልብህ ታምናለህ።

ለመንፈሳዊ ሕይወት አዲስ ስትሆን ገና ጥቂት ጸልየህ፣ ጥቂት ጾመህ፣ ጥቂት መጽውተህ ሳለ ግን ሩጫህን ወደ መጨረሱ የተቃረብህ ይመስልሃል። ጉዞህን በግማሽ እርምጃ ከመጀመርህ ከፍጻሜው ላይ የደረስህ ያህል ይሰማሃል። "እኔን ምሰሉ" ማለት ያምርሃል። ነገር ግን መንፈሳዊ ሕይወት የቱንም ያህል ብትሮጥበት ሁል ጊዜ እንደ ጀማሪ የሚያደርግ ረጅም ጎዳና ነው። ሰማንያ ዓመት በገዳም ሲጋደል የነበረው አባ ሲሶይ ነፍሱ ከሥጋው ልትለይ በቀረበች ጊዜ ብዙ መነኮሳት በአልጋው ዙሪያ ከበውት ሳለ ቅዱሱ "አምላኬ ሆይ፣ እባክህ ለንስሐ የሚሆን ጥቂት ጊዜን ስጠኝ?" እያለ በልቅሶ ሲማጸን ሰሙት። በዚህ የተገረሙት መነኮሳቱ አባ ሲሶይን "አባታችን አንተ እድሜ ልክህን በንስሐ የኖርህ መምህረ ንስሐ ሆነህ ሳለ እንዴት አሁን ጥቂት የንስሐ ጊዜን ትለምናለህ?" ቢሉት፣ ቅዱሱም "ልጆቼ ይህን መንፈሳዊ ጥበብ (ንስሐን) ገና አሁን መጀመሬ ነው" አላቸው።

ጌታ ሆይ መንፈሳዊ ሕይወት እኖር ዘንድ አስጀምረኝ፤ ገና ጀማሪ ሳለሁ ደርሻለሁ ከማለትም ሰውረኝ። እንድቆም አትፍቀድልኝ፤ ወደ አንተ ሳበኝ፣ አሳድገኝ። ብለን ሁልጊዜ መጸለይ ይገባናል።
እግዚአብሔር አምላክ ለንስሐ ሞት ያብቃን። ንስሐ የምንገባበት ጥቂት የንስሐ ዕድሜ ለሁላችንም ያድለን።
ብሒላተ አበው ወእመት ዘኦርቶዶክስ ተዋሕዶ pinned «የበኩረ መዘምራን ኪነ ጥበብ የዩቲዩብ ቻናል ነው ተብለናል ። የቀደሙት መዝሙራት በነበሩበት ቅጂ ቀርበዋል። ከመዝሙራቱ ጥዑምነት ባለፈ በረከትና ለታላቁ ትሑት አገልጋይ ወንድማችን ፍቅራችንን መግለጫ ይሆነናልና Subscribe እናድርግ። https://youtu.be/3ZflOHprp5g?si=IYnd3rs1MnlpfKfX»
የልብን ከሰይጣን።
.
ቀደምት አበው እና እማት የሰይጣንን ማንነት በሚገባ ከማወቃቸው የተነሣ ሰይጣንን መዋጋት እና ማሸነፍ ብቻ ሳይሆን ሰይጣንን ራሱን ያታልሉት ነበር። ይህም መንፈሳዊ ብቃታቸው እና ዕውቀታቸው የቱን ያህል ይደርስ እንደነበረ ከሚመሰክሩት ነገሮች አንዱ ነው። የትምህርተ-ኅቡዓት መተርጉማን «ሰይጣን የተነገረውን እንጂ የታሰበውን አያውቀውም» ይላሉ። ሰይጣን የሚችለው በሰው ልቡና የታሰበውን መገመት ብቻ ነው። በሰው ልቡና የተመላለሰውን ማወቅ ስለማይችል ሰዎች የልባቸውን ሁሉ እንዲናገሩ ይገፋፋቸዋል። ሔዋንን ስለዕጸበለስ ያንን ሁሉ የጠየቃት ለማወቅ ወይንም ለመረዳት ፈልጎ ሳይሆን ሥላሴ በሔዋን ልቡና የጻፉትን ነገር ማወቅ ስላልቻለ ነው። ሔዋን ስትናገር ግን ሃሳቡን ዐወቀ። ዐውቆም ዝም አላለም፤ ጠልፎ የሚጥልበትን ወጥመድ አዘጋጀ። እናቶቻችን ወደ ቅዱሳት መካናት ለመሳለም ሲሄዱ «ላሊበላ፣ አኩስም፣ ግሼን ልሄድ ነው» አይሉም ነበር። «እንጨት ልሰብር፣ ውኃ ልቀዳ፣ ዘመድ ልጠይቅ» እያሉ ነበር የሚጓዙት። ይህም ሰይጣን በልቡናቸው ያለውን ተረድቶ ዕንቅፋት እንዳያመጣባቸው ነው። ይህንን የሰይጣን ስንፍና ከሚያውቁ አበው መካከል አባ ሉቃ እና አባ ታድራ ያደረጉትን ከመጽሐፈ-መነኰሳት አንዱ የሆነው መጽሐፈ-ፊልክስዮስ ክፍል ፬ ተስእሎ ፶፮ ገጽ 91 ላይ እንዲህ ይነግረናል።
በአንድ ገዳም ውስጥ አባ ታድራ እና አባ ሉቃ የሚባሉ መነኰሳት ነበሩ። “እንጸናለን” ብለው የመጡ ብዙ መነኰሳትን ሰይጣን ከበኣታቸው ሲያስወጣቸው ተመለከቱና እንዲሁ ውስጥ ለውስጥ ተግባቡ። «በቀጣዩ ክረምት ከበኣታችን ወጥተን በበረሃ ለብቻችን እንጋደላለን፤ በዚያም ሰይጣንን ድል እናደርገዋለን» ተባባሉ። ሰይጣንም እውነት መስሎት እነርሱን ከበኣታቸው ለማውጣት የሚያደርገውን ፈተና ተወው። በበረሃም ይጠብቃቸው ጀመር። ክረምት በደረሰ ጊዜም «አሁንማ በክረምት እንዴት እንሄዳለን፤ በጋ ሲወጣ በረሃ ወርደን ሰይጣንን እንቀጠቅጠዋለን፣ እስከዚያ ዝም ብለን እንቀመጥ» ተባባሉ። ሰይጣንም እውነት መስሎት ፈተናውን ሁሉ ትቶ በጋ እስኪደርስ ጠበቃቸው። በጋም በደረሰ ጊዜ «ወደ በረሃ እንሄዳለን ተባብለን’ኮ ሰነፍን፣ ምን ይሻላል? በቃ በክረምት እንሄዳለን» ተባባሉ።
እንዲህ እያሉ ሰይጣንን ሃምሳ ስድስት ዓመት ዘበቱበት። በዚህም የተነሣ የመልክአ-ሥላሴ ደራሲ እንዲህ የሚል አርኬ ደረሰላቸው:
ሰላም ለአክናፊክሙ እሳታውያን አክናፍ፤
እለበማእከል ሀለዉ ወእለሀለዉ በጽንፍ፤
አለብወኒ ሥላሴ ቀትለ-መስተጋድል መጽሐፍ፤
ከመ-ወትረ ይትዋሥአኒ ትምይንተ-ሉቃ ትሩፍ፤
ወጉሕሉተ-ታድራ ምስሌየ ይዛዋዕ በአፍ።
በጎ ነገሮችን ከሰው ተማክሮ መሥራት መልካም ነው። ነገር ግን ቆራጥነትን የሚጠይቁ፣ ፈተናም የሚበዛባቸውን መልካም ነገሮችን ከመሥራት በፊት ማውራት ግን በራስ ፈቃድ መከራ መጋበዝ ነው። አበው እንዳሉት ሰይጣን የተነገረውን እንጂ የታሰበውን አያውቅም። ስለዚህም ስለምናስበው ነገር ሁሉ በየአጋጣሚው እንድናወራ ያደርገናል። ሥራን አንደበት ከሚገልጠው ራሱ ሥራው ራሱን ቢገልጥ እንዴት የተሻለ ነው? ብዙ እያወሩ ጥቂት ከመሥራት፣ ምንም ሳያወሩ ብዙ መሥራት እንዴት መልካም ነው? “ሙያ በልብ ነው” ይላል የሀገሬ ሰው። በየትዳሩ፣ በየማኅበሩ፣ በየጉባኤው፣ በየአጥቢያው ፈተና ከሚበዛባቸው ምክንያቶች አንዱ ይኼ ሊሆንስ ከቻለ? ሁሉንም ነገር ለሰይጣን ስለምንነግረው። ባል እና ሚስት ተያይተው ብቻ የሚግባቡባቸውን መንገዶች ገንዘብ ማድረግ አለባቸው። የምናስበውን ሁሉ አናውራ። በልቡናችን ተቀምጦ በተግባር ብቻ መገለጥ ያለበትን እንለይ።
ኮሚቴ ሲበዛ፣ ስብሰባ ሲበዛ፣ ውይይት ሲበዛ፣ ሰው ሲበዛ ብዙ ጊዜ መንፈሳዊ ሥራ መስራት ከባድ ይሆናል፤ መሰናክሉም ይበዛል። አንዳንድ ጊዜ ከተሰብሳቢዎቹ ጋር አጅሬም አብሮ ሳይሰበሰብ አይቀርም። ሴት የበዛበት ወጥ እና ወሬ የበዛበት መንፈሳዊ ሥራ ሁለቱም ይበላሻሉ። እስኪ ከወሬ ተግባር ይቅደም። የነአባ ታድራን እና የነአባ ሉቃን ነገር ባንረሳው መልካም ነው።

ስማችሁ የለም" ከተሰኘው መጽኃፍ የተወሰደ
༻༺✟"ክብሩ በአንቺ ላይ ይታያል"✟༺
. ༻༺✟ኢሳ.60፥2 ✟༻༺
በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሀዱ አምላክ አሜን!

በቅድምያ እንኳን ለእመቤታችን ለቅድስት ድንግል ማርያም ዓመታዊ ክብረ በዓል በሰላምና በጤና አደረሳችሁ
አደረሰን!

እንደ ሚታወቀው ግንቦት ሃያ አንድ ቀን በዚች ዕለት አምላክን የወለደች እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም በደብረ ምጥማቅ በስሟ በተሠራች ቤተ ክርስቲያን ጉልላት ላይ በብርሃን መርከብ ተቀምጣ፤ በልጅዋ የመለኮት ብርሃን ተጎናፅፋ፤
የመላእክት ሠራዊት
የመላእክት አለቆች በየማዕረጋቸው ክንፋቸውን ዘርግተው በዙሪያዋ ቆመው ፊቷ በግልጥ ስለመታየቱ የክርስቲያን ወገኖች ሁሉ ታላቅ በዓልን ያደርጋሉ ።

ግልፅ በሆነ አማርኛ እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም የእግዚአብሔር የክብሩ መገለጫ ናት።

ስለዚህ እንዲህ ነው ብሎ ለማስረዳት እንኳ በሚያስቸግር መልኩ የእግዚአብሔር ክብሩ በእርሷ ላይ ተገለጠ።

እርሷ በብልሃተኛ እጅ ያልተሠራች ከብርሃን የተገኘው ራሱ የአብ ብርሃን በእርሷ ላይ አድሮ በአምላክነቱ ለዓለም ሁሉ ያበራባት የወርቅ መቅረዝ ምሳሌ ናት።

በእርሷ ላይ ክብሩን ገልጦ
ጨለማን ከሰዎች ላይ ያራቀውና
"እኔ የዓለም ብርሃን ነኝ፤
በብርሃኔ እመኑ፤
ብርሃን ሳለላችሁ ተመላለሱ"
ብሎ በሚያድን ቃሉ ያዳነን ደግሞ እርሱ ኢየሱስ ክርስቶስ ነው።

ድንግል ማርያም እንደ መስታወት ናት።
መስታወት በራሱ በተፈጥሮው ብርሃን የለውም።
የፀሐይ ብርሃን ሲበራበት ግን የሁሉም ሰው ዓይን ሊቋቋመው በማይችል መልኩ መስታወቱ በሩቅ ያንፀባርቃል።

እመቤታችን ድንግል ማርያምም ከሐና እና ከኢያቄም የተወለደች የሰው ዘር ናት።

ነግር ግን ፀሐየ ጽድቅ ክርስቶስ ብርሃኑን በእርሷ ላይ ስለ አበራባት
ንጽሕናዋ፣
ቅድስናዋ፣
ድንግልናዋ፣
እናትነቷ ሁሉ ዓለም አቀፋዊ ነፀብራቅ ሆነ።

እርሱ ክብሩን ስለገለጠባት
የእርሷ ክብሯ ገነነ።

እርሱ ስለ ወደዳት
እርሷ በትውልድ ሁሉ ዘንድ ተወደደች።

እርሱ ከፍ ከፍ ስለ አደረጋት
የእርሷ ከፍታ ከከፍታዎች ሁሉ በላይ ሆነ።

በደብረ ምጥማቅ ከተማ ላይ የተገለጠውም እውነት ይኸው ነበር።

እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያምን በቤተ ክርስቲያን ጉልላት ላይ የልጅ ዓይን ወደ እናቷ ትኩር ብላ እንደምትመለከት ያመኑትም ያላመኑትም ብርሃንን ለብሳ ብርሃንን ተጎናጽፋ አምስት ቀን ሙሉ ተሰልፈው ሲያይዋት ሰነበቱ።

"ሰላም ለእለ ርእዩኪ ከመ ዐይነ ወለት ኀበ እማ፤ መዋዕል ሐምስ እስከ ይትፌጸማ፤
ማርያም ንግሥት ውስተ ደብረ ምጥማቅ ከተማ፤ ብፁዓት አዕይንት ዘነጸራኪ በግርማ፤
ወብፁዓት አእጋር ቅድሜኪ ዘቆማ።"
እንዳለ አርኬ።

ሰማያውያን መላእክት ከብበዋት ብርሃን ለብሳ ብርሃን ተጎናፅፋ በሚያስደንቅ ግርማ ሆና ትልቁም ትንሹም ወንዱም ሴቱም አምስት ቀን ሙሉ በዚያው ሥፍራ ላይ ድንኳን ተክለው አጎበር ጥለው በግልጥ እየተመለከቷት በዓል ሲያደርጉ ሰነበቱ።

ዛሬ ግን ጉዳዩ ከደብረ ምጥማቅም አልፎ በመላው ዓለም በዓሉ በደማቅ ሁኔታ ሲከበር ይኖራል።

የእመቤታችን የቅድስት ድንግል ማርያም ጉዳይ ይህን ያህል እንዲህ በክርስቲያኖች ሕይወት ውስጥ ሥር ሰድዶ ትልቅ ትኩረት ሊያገኝ የቻለው ደግሞ ኢሳይያስ በነገረን መልኩ እግዚአብሔር ክብሩን በእርሷ ላይ ስለ ገለጠ ነው።

ወዳጄ እግዚአብሔር እንዲህ ክብሩን ሲገልጥብህና አንተም የክብሩ መገለጫ ስትሆን ለዓለም ሁሉ መነጋገርያ አጀንዳ ትሆናለህ።

እግዚአብሔር ከፍ ሲያደርግህ ቀና ብሎ አንተን ለማየት የማይጓጓ ፍጥረት የለም።

እግዚአብሔር ስምህን ሲባርከው የስምህ መዓዛ ከልበኔ፣ ቁስጥ እና ሰንበልት ከሚባሉት ሽቱዎች በላይ ዓለምን ሁሉ የሚያውድ ግሩም የሆነ መዓዛ ይኖረዋል።

እኛም ዛሬ በምስጋና ማማ ላይ ሆነን፦
"ሰላም ሰላም ለዝክረ ስምኪ ሐዋዝ፣
እምነ ከልበኔ ወቀስጥ ወእምነ ሰንበልት ምዑዝ፣..."
እያልን የድንግል ማርያምን ስም በክብር የምናነሳበት ትልቁ ምሥጢር ይኸው ነው።

ድንግል ማርያምን ሁል ጊዜ ትውልድ ሁሉ ብፅዕት የሚላት ብርቱ የሆነ እርሱ እግዚአብሔር በእርሷ ላይ ታላቅ ሥራን አድርጎአልና ነው።
እርሷ ራሷ "እስመ ገብረ ሊተ ኃይለ ዓቢያተ" እንዳለች።
ሉቃ.1፥49

ይህ እግዚአብሔር በእርሷ ላይ ያደረገው ታላቁ ሥራም ክብሩን በእርሷ ላይ የገለጠበቱ ረቂቅ ምሥጢር ነው።

ስለዚህ እግዚአብሔር ክብሩን የገለጠባትን ድንግል ማርያምን እግዚአብሔር ባከበራት ክብር ስናከብራት እንኖራለን።

የክብር ባለቤት የሆነውን እግዚአብሔርን ደግሞ ለዘለዓለም እናመልካለን።

አሜን!!!

╭✥✥✥✥✥✥✥✥✥╮
✥┈┈••●◉✞◉●••┈••✥
. አባ ኒቆዲሞስ (ጳጳስ)
. 21/09/2016 ዓ.ም
. ከሕይወት ተራራ ላይ
✥┈┈••●◉✞◉●••┈┈✥
╰✥✥✥✥✥✥✥✥✥╯
"አርእይኒ ገጸ ዚአኪ ማርያም ምእረ፤ ዘኢይሰምዖ ካልዕ እንግርኪ ነገረ"
"ማርያም ሆይ፣ ለሌላው የማልነግረውን ነገር እነግርሽ ዘንድ አንድ ጊዜ ፊትሽን አሳይኝ"

መልክአ ማርያም

እንኳን ለበዓለ ደብረ ምጥማቅ በሰላም አደረሳችሁ!
የክርስቲያናዊ ጋብቻ መገለጫዎች

አንድነት ፦
ቤተክርስትያን የምታስተምረው የጋብቻ ትምህርት አንድ ወንድ ለአንድ ሴት የሚባለውን ነው በመጀመሪያ እግዚአብሔር ያዘጋጅው አንድ አዳምን ለአዲት ሄዋን ነውና። በሥርዓተ ተክሊል እና በቅዱስ ቁርባን ሁለት የነበሩት ተጋቢዎች በክርስቶስ አንድ ይሆናሉ ስለዚህም ወደ ፊትም አንድ እንጂ ሁለት አይባሉም። ስው አባትና እናቱን ይተዋል ከሚስቱም ጋር ይተባበራል ሁለቱም አንድ ሥጋ ይሆናሉ (ኤፌ 5፥21)

ዘላቂነት ፦
ጋብቻ ሁለቱ ጥንዶች ያለ መለያየት እስከ እድሜያቸው ፍጻሜ በአንድነት የሚቆዩበት ሕይወት ነው። ምናልባት ሊለያዩባቸው የሚችሉበት ምክንያቶች ይኖራሉ ከነዚህም ውስጥ:-
* አንዱ ዝሙት ነው ይህም የመለያያ ምክንያት የሚሆነው የቅዱስ ጋብቻ ቅድስና ስለሚያሳድፈው ነው። ነገር ግን ኃጥያቱን የሠራው ወገን ንስሃ ከገባ እና ይቅር ከተባባሉ አብረው እንዲቀጥሉ ቤተክርስትያን ታስተምራለች ።
ሁለተኛው ፍቺ ሊፈፀም የሚችልበት ምክንያት ከሁለት አንዳቸው እምነታቸውን (ሃይማኖታቸውን) የለወጡ ከሆነ ወይም አለመመሳሰል (ልዩነት) ሲኖር ነው።
*
ሦስተኛው ጋብቻ የሚፈርስበት ምክንያት ባል ወይም ሚስት ከሁለት አንዳቸው በሞት ሲለዩ ነው።

ፍሬ ማፍራት ፦
በመንፈስ ቅዱስ ረዳትነት በቅዱስ ጋብቻ ሕይወታቸውን የሚመሩ ጥንዶች በርካታ ፍሬዎችን ያፈራሉ። ፍሬዎቻቸውም ፍቅር፣ በጎነት፣ የቤተክርስትያን አገልግሎት እንዲሁም ልጆች ናቸው።

ማጠቃለያ ፦የጋብቻ ሕይወት ጥንዶች በንፅህናና በቅድስና ሆነው በጋራ መንፈሳዊ ሕይወታቸውን በመምራት ክርስትያናዊ ተጋድሎ እየፈፀሙ ራሳቸውን ለመንግስተ እግዚአብሔር የሚያዘጋጁበት ሕይወት ነው። በተጨማሪም እግዚአብሔርን የሚያገለግሉ ሃገርን የሚጠቅሙ ልጆችን ወልደው በአግባቡ በማሳደግ በስርዓት የሚያንፁበት ሕይወት ነው።
ስለዚህ ከጋብቻ በፊት ይህንን ኃላፊነት ለመወጣት በቂ ስነ ልቦናዊና መንፈሳዊ ዝግጅትና ምክር ያስፈልጋልና ወደ አባቶች ቀርበን ልንማርና ልምድ ልንወስድ ያስፈልገናል።

(afa-የኦርቶዶክስ ተዋህዶ ፍሬ page ላይ የተወሰደ)
“ክርስቲያን” ተብለህ መጠራትህ ዋስትና አይኾንህም፤ ዋስትና የሚኾንህ …

በመንገድ ዳር ላይ ዘርን የሚዘሩ ሰዎች ምንም የሚያገኙት ጥቅም እንደ ሌለ ኹሉ፥ እኛም ለልጅነታችን የሚገባ’ ምግባር ከሌለን ክርስቲያኖች ተብለን ከመጠራት የምናገኘው በቁዔት የለም፡፡ ይህ እንዴት ይኾናል የምትለኝ ከኾነም የጌታችን ወንድም የተባለው ያዕቆብን ምስክር አድርጌ እነግርሃለሁ፡፡ እርሱ፡- “ሥራ የሌለው እምነት ቢኖር በራሱ የሞተ ነው” ብሎአልና (ያዕ.2፡17)፡፡ ስለዚህ ለእኛ (ለክርስቲያኖች) ምግባር መያዝ ግዴታ ነው፡፡ ምግባር ከሌለን ግን “ክርስቲያን” የሚለው ስም ለእኛ የሚፈይደው ምንም ነገር የለም፡፡ በዚህ ተደነቅህን? እንኪያስ ንገረኝ ! በዓውደ ውጊያ የማይሳተፍ፣ ለሚመግበው ንጉሥም የማይዋጋ ከኾነ አንድ ወታደር ወታደር ተብሎ ቢጠራ ምን ጥቅም አለው? ለንጉሡ ክብር የማይዋጋ ከኾነስ ወታደር ተብሎ ባይጠራ ይሻለዋል፡፡ ይህ ሰው በንጉሡ የሚመገብ ኾኖ እያለ፥ ነገር ግን ንጉሡ በጠላቱ ላይ ድል እንዲያደርግ የማይዋጋ ከኾነ እንዴት ከቅጣት ሊያመልጥ ይችላል? ንጉሡን ምሳሌ አድርጌ ልናገረው የፈለግሁትስ ምንድን ነው? ልለው የፈልገሁት እግዚአብሔር በትንሹ ስለ ገዛ ነፍሳችን እንድንጠነቀቅ (ምግባር መያዝ እንድንችል) ኃይል (ዓቅም) ሰጥቶናል ነው፡፡

ቅዱስ ዮሐንስ አፈወርቅ፣ ንስሐና ምጽዋት መጽሐፍ
2024/06/02 12:27:50
Back to Top
HTML Embed Code: