††† እንኳን ለዘመነ ሐጋይ (በጋ) የመጨረሻ ዕለትና ለሐዋርያው ቅዱስ አንሲፎሮስ በዓለ ዕረፍት በሰላም አደረሳችሁ፤ አደረሰን። †††

††† በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን! †††

††† አምላካችን እግዚአብሔር ሁሉን ስነ ፍጥረት የፈጠረ ለሰው ልጆች ጥቅም ነው:: ጌታ አዝማናትን : ወሮችን : ሳምንታትን : ቀኖችንና ሰዓታትን ፈጥሮ : ወስኖ ሰጥቶናል:: የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ጥንታዊት እንደ መሆኗ ሁሉ ነገሯ በሥርዓት ይፈፀማል::

በራሷ የዘመን ቀመር ስሌት መሠረትም አንድ ዓመት በአራት ወቅቶች ይከፈላል:: አባታችን ሊቁ ቅዱስ ያሬድም እነዚህን ወቅቶች መሠረት አድርጎ መንፈሳዊ ድርሰቶችን ደርሷል::

እነዚሕ አዝማናት (ወቅቶች):-
1.ዘመነ ክረምት (ከሰኔ 26 እስከ መስከረም 25)
2.ዘመነ መፀው (ከመስከረም 26 እስከ ታኅሣሥ 25)
3.ዘመነ ሐጋይ (ከታኅሣሥ 26 እስከ መጋቢት 25)
4.ዘመነ ፀደይ (ከመጋቢት 26 እስከ ሰኔ 25) መሆናቸው ይታወቃል::

ዘመነ ሐጋይ (በጋን) የባረከ አምላክ ዘመነ ፀደይ (መከርን) እንዲባርክልን : የንስሐ ጊዜም እንዲያደርግልን ቅዱስ ፈቃዱ ይሁን::

††† ቅዱስ አንሲፎሮስ †††

††† በዚህች ዕለት ጌታችንን በሃገረ ናይን የተከተለ : ከዋለበት ውሎ : ካደረበት ያደረ : ከሰባ ሁለቱ አርድእት የተቆጠረ ሐዋርያው ቅዱስ አንሲፎሮስ አርፏል::

††† ዳግመኛ በዚህ ዕለት አይሁድ ለመጨረሻ ጊዜ ጌታችንን ሊገድሉት ተስማሙ:: ይሁዳም በ30 ብር ይሸጠው ዘንድ ከአይሁድ ጋር ተዋዋለ::

††† የጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ይቅርታውና ምሕረቱ ከሁላችን ጋር ይሁን::

††† መጋቢት 25 ቀን የሚከበሩ ዓመታዊ የቅዱሳን በዓላት
1.ቅዱስ አንሲፎሮስ ሐዋርያ (ከሰባ ሁለቱ አርድእት)

††† ወርኀዊ በዓላት
1.ቅዱስ መርቆሬዎስ ሰማዕት
2.ቅድስት ቴክላ ሐዋርያዊት
3.ቅዱስ አበከረዙን ሰማዕት
4.ቅዱስ ዱማድዮስ ሶርያዊ
5.አቡነ አቢብ (አባ ቡላ)
6.ቅዱስ አባ አቡፋና ጻድቅ

††† "ከጥንት ጀምሮ እግዚአብሔር በብዙ ዓይነትና በብዙ ጐዳና ለአባቶቻችን በነቢያት ተናግሮ: ሁሉን ወራሽ ባደረገው ደግሞም ዘመናትን በፈጠረበት በልጁ በዚህ ዘመን መጨረሻ ለእኛ ተናገረን:: እርሱም . . . ኃጢአታችንን በራሱ ካነጻ በኋላ በሰማያት በግርማው ቀኝ ተቀመጠ::" †††
(ዕብ. ፩፥፩)

††† ወስብሐት ለእግዚአብሔር †††
††† እንኳን ለጥንተ በዓለ ምሴተ ሐሙስ እና ኢዮጰራቅስያ ድንግል ዓመታዊ በዓል በሰላም አደረሳችሁ፤ አደረሰን። †††

††† በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን! †††

††† ምሴተ ሐሙስ †††

††† ስም አጠራሩ ከፍ ከፍ ይበልና መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ከ1978 ዓመታት በፊት "ምሴተ ሐሙስ" በምትባለው በዚሕች ዕለት:-
1.በወዳጁ በዓልዓዛር ቤት የዓለማት ፈጣሪ ሲሆን በትሕትና ዝቅ ብሎ የደቀ መዛሙርቱን እግር አጥቧል::
2.ለእኛ ድኅነት ይሆነን ዘንድ ቅዱስ ሥጋውን : ክቡር ደሙን ለመጀመሪያ ጊዜ ሰጥቷል::
3.በጌቴሴማኒ ላበቱ እንደ ደም እየተንጠፈጠፈ ጸልዮ "ወደ ፈተና እንዳትገቡ ጸልዩ" ሲል አስተምሯል::
4.ምሽት 3 ሰዓት አካባቢ ይሁዳ ሊቃነ ካህናቱን አስከትሎ መጥቶ ለ30 ብር አሳልፎ ሰጥቶታል:: (ማቴ. 26:26 / ዮሐ. 13:1)

ይሕ ሁሉ ለእኛ ድኅነት ተፈጽሟልና ምስጋናና ክብር ለፈጣሪያችን ኢየሱስ ክርስቶስ ይሁን::

††† ኢዮጰራቅስያ ድንግል †††

††† ዳግመኛ በዚህ ዕለት እናታችን ቅድስት ኢዮጰራቅስያ ድንግል አርፋለች::

ቅድስቲቱ በ5ኛው መቶ ክ/ዘመን የነበረች እናት ስትሆን ገና በ9 ዓመቷ ምድራዊ ሐብትን ንቃ መንናለች:: ምክንያቱም ዘመዶቿ የሮም ነገሥታት እነ አኖሬዎስ ነበሩና:: ድንግል ኢዮጰራቅስያ በገዳም : በጾምና በጸሎት : በፍፁም ትሕትናና ታዛዥነት : እንዲሁም በፍቅር ኑራ በዚህች ቀን አርፋለች::

††† ከቅድስት እናታችን በረከት አምላኩዋ ይክፈለን::

††† መጋቢት 26 ቀን የሚከበሩ ዓመታዊ የቅዱሳን በዓላት
1.ቅዱሳን ሐዋርያት
2.ቅድስት ድንግል ኢዮጰራቅስያ
3.ቅዱስ ፍርፍርዮስ ሰማዕት

††† ወርሐዊ በዓላት
1.ቅዱስ ቶማስ ሐዋርያ
2.አቡነ ሐብተ ማርያም ጻድቅ
3.አቡነ ኢየሱስ ሞዐ ዘሐይቅ
4.ቅዱሳን ሰማዕታተ ናግራን
5.አቡነ ሰላማ ከሣቴ ብርሃን

††† "ሥጋዬን የሚበላ ደሜንም የሚጠጣ የዘለዓለም ሕይወት አለው:: እኔም በመጨረሻው ቀን አስነሳዋለሁ:: ሥጋዬ እውነተኛ መብል: ደሜም እውነተኛ መጠጥ ነውና:: ሥጋዬን የሚበላ ደሜንም የሚጠጣ በእኔ ይኖራል:: እኔም በርሱ እኖራለሁ::" †††
(ዮሐ. 6:53-56)

††† "እግራቸውን አጥቦ: ልብሱንም አንስቶ ዳግመኛ ተቀመጠ:: እንዲሕም አላቸው:- 'ያደረግሁላችሁን ታስተውላላችሁን? እናንተ መምሕርና ጌታ ትሉኛላችሁ:: እንዲሁ ነኝና መልካም ትላላችሁ:: እንግዲህ እኔ ጌታና መምሕር ስሆን እግራችሁን ካጠብሁ እናንተ ደግሞ እርስ በርሳችሁ እግራችሁን ትተጣጠቡ ዘንድ ይገባል::' " †††
(ዮሐ. 13:12-14)

††† ወስብሐት ለእግዚአብሔር †††
††† እንኳን ለጌታችንና አምላካችን መድኃኔ ዓለም ኢየሱስ ክርስቶስ ዓመታዊ የስቅለት በዓል በሰላም አደረሳችሁ፤ አደረሰን። †††

††† በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን! †††

††† መድኃኔ ዓለም †††

††† ጌታችን መድኃኔ ዓለም ክርስቶስ ለእኛ ሲል በፈጸመው የማዳን ሥራ በዚሕ ዕለት ክፉዎች አይሁድ ከምሽቱ 3:00 ጌቴሴማኒ ውስጥ ያዙት::
ሙሉውን ሌሊት ከቀያፋ ወደ ሐና: ከሐና ወደ ቀያፋ ሲያመላልሱት: አስረው ሲደበድቡት አድረዋል::

*ዝም ቢላቸው ዓይኑን ሸፍነው በጥፊ መቱት:: ምራቃቸውን ተፉበት:: ዘበቱበት:: ራሱንም በዘንግ መቱት:: እርሱ ግን ሁሉን ታገሰ::

*በጧት ከገዢው ዘንድ ሞት እንዲፈረድበት አቀረቡት:: በሠለስት (ሦስት ሰዓት ላይ) አካሉ እስኪያልቅ እየተዘባበቱ 6,666 ገረፉት:: ሊቶስጥሮስ አደባባይ ላይ እርጥብ መስቀል አሸክመው ወደ ቀራንዮ ወሰዱት::

*ስድስት ሰዓት ላይ በረዣዥም ብረቶች አምስት ቦታ ላይ ቸንክረው ሰቀሉት:: ሰባት ታላላቅ ተአምራት በምድርና በሰማይ ታዩ::
ዓለም በጨለማ ሳለች ጌታ በመስቀል ላይ ሰባት ቃላትን ተናገረ::

*ከቀኑ ዘጠኝ ሰዓት ላይ በባሕርይ ሥልጣኑ ቅድስት ነፍሱን ከቅዱስ ሥጋው ለየ:: በዚያች ሰዓትም ወደ ሲዖል ወርዶ የታሠሩትን ሁሉ ፈታ:: አሥራ አንድ ሰዓት ላይ ደጋጉ ዮሴፍና ኒቆዲሞስ ከታላቅ ክብርና ሐዘን ጋር በአዲስ መቃብር ቀበሩት::

*በዚያች ቀን ድንግል ማርያም ልቧ በሐዘን ተቃጠለ:: ወዳጁ ቅዱስ ዮሐንስም ፍፁም ለቅሶን አለቀሰ:: ቅዱሳት አንስት በዋይታ ዋሉ:: (ማቴ. 27:1, ማር. 15:1, ሉቃ. 23:1, ዮሐ. 19:1)

††† ለእኛ ለኀጥአን ፍጡሮቹ ሲል ይህንን ሁሉ መከራ የታገሰ አምላክ ስለ አሥራ ሦስቱ ኅማማቱ: አምስቱ ቅንዋቱ: ስለ ቅዱስ መስቀሉ: ስለ ድንግል እናቱ ለቅሶና ስለ ወዳጁ ቅዱስ ዮሐንስ ብሎ ይማረን::

††† ከቅዱሳኑ በዚሕች ዕለት:-

††† ከ80 ዓመታት በላይ በገዳም የኖረ: የገዳማውያን ሞገሳቸው: የመነኮሳትም ሁሉ አለቃ ታላቁ ቅዱስ መቃርስ አርፏል::

††† ዳግመኛ በዚህ ቀን ንግሥናን ከሊቅነት: ጽድቅን ከሰማዕትነት ጋር የደረበው ሰማዕቱ ቅዱስ ገላውዴዎስ አንገቱን ተከልሏል:: ቅዱስ ገላውዴዎስ የጻድቁ ዐፄ ልብነ ድንግል ልጅ ነው::

††† መድኃኔ ዓለም ከወዳጆቹ ጸጋ ክብርን ያድለን::

††† መጋቢት 27 ቀን የሚከበሩ ዓመታዊ የቅዱሳን በዓላት
1.ቅዱስ ዮሐንስ (ፍቁረ እግዚእ)
2.ቅዱሳት አንስት (ከእግረ መስቀሉ ያልተለዩ)
3.ቅዱሳን ባልንጀሮች (በጌታ ስቅለት ጊዜ ከሞት የተነሱ)
4.ቅዱሳን ዮሴፍና ኒቆዲሞስ
5.ታላቁ ቅዱስ መቃርስ (የመነኮሳት አለቃ)
6.ማር ገላውዴዎስ ሰማዕት (የኢትዮዽያ ንጉሥ)
7.ቅዱስ ዕፀ መስቀል

††† ወርኀዊ በዓላት
1.አቡነ መብዐ ፅዮን ጻድቅ
2.ቅዱስ ፊቅጦር ሰማዕት
3.ቅዱስ ያዕቆብ ዘግሙድ
4.ቅዱስ ቢፋሞን ጻድቅና ሰማዕት

††† "የተጠራችሁለት ለዚህ ነው:: ክርስቶስ ደግሞ ፍለጋውን እንድትከተሉ ምሳሌ ትቶላችሁ ስለ እናንተ መከራን ተቀብሏልና:: እርሱም ኃጢአት አላደረገም:: ተንኮልም በአፉ አልተገኘበትም:: ሲሰድቡት መልሶ አልተሳደበም:: መከራንም ሲቀበል አልዛተም . . . እርሱ ራሱ በሥጋው ኃጢአታችንን በእንጨት ላይ ተሸከመ::" †††
(፩ጴጥ. ፪፥፳፩-፳፭)

††† ወስብሐት ለእግዚአብሔር †††
††† እንኳን ለታላቁ ክርስቲያናዊ ንጉሥ ቅዱስ ቆስጠንጢኖስ ዓመታዊ የዕረፍት በዓል በሰላም አደረሳችሁ፤ አደረሰን። †††

††† በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን! †††

††† ቅዱስ ቆስጠንጢኖስ †††

††† ቅዱስ ቆስጠንጢኖስ ለቤተ ክርስቲያን የፈፀመውን መልካም ተግባር ያሕል መሥራት የቻለ ንጉሥ በሐዲስ ኪዳን የለም:: ጻድቁ ንጉሥ ከቅድስት እናቱ እሌኒና ከአረማዊ አባቱ ቁንስጣ በበራንጥያ ተወለደ::

ዘመኑ ዘመነ ዐጸባ (የመከራ ጊዜ) ወይም የሰማዕታት ዘመን በመሆኑ ክርስቲያኖች በግፍ የሚጨፈጨፉበት ወቅት ነበር:: ክርስቲያኖችን ከምድረ ገፅ ለማጥፋት በተደረገው የ40 ዓመታት ዘመቻ አብያተ መቃድስና መጻሕፍት ተቃጠሉ:: ብዙዎቹ በየበርሃው ተሰደዱ:: ሚሊየኖች በግፍ አለቁ::

የዚሕን ዘመን መከራ በውል ያልተረዳ ሰው ቅዱስ ቆስጠንጢኖስን ሊያከብር አይችልም:: ምክንያቱም ይህን የመከራ ዘመን በፈቃደ እግዚአብሔር አስቁሞ : ቀርነ ሃይማኖት የቆመው : ብዙ ሥርዓት የተሠራው : ቤተ ክርስቲያንም ያበራችው በዘመኑ ነውና::

ቅዱሱ ንጉሥ ለሁሉም ነቢያት : ሐዋርያትና ሰማዕታት አብያተ ክርስቲያናትን ራሱ በመሠረታት በቁስጥንጥንያ አንጿል:: በዘመኑ ቤተ ክርስቲያን በሰላም ኖራለት : በኃይለ መስቀሉ ጠላት ጠፍቶለት ኑሮ በዚህች ቀን አርፏል:: "ቆስጠንጢኖስ" ማለት "ሐመልማል" ማለት ነው::

††† ዳግመኛ በዚሕ ቀን የዓለማት ፈጣሪ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ስለ እኛ በሆነው ሞቱ በመቃብር ውስጥ አድሯል::

††† ጌትነት ያለው አምላካችን በይቅርታው ይጐብኘን:: መልካም መሪንም ይስጠን::

††† መጋቢት 28 ቀን የሚከበሩ ዓመታዊ የቅዱሳን በዓላት
1.ታላቁ ቅዱስ ቆስጠንጢኖስ (ጻድቅ ንጉሥ)
2.ቅድስት እሌኒ ንግስት

††† ወርኀዊ በዓላት
1.አማኑኤል ቸር አምላካችን
2.ቅዱሳን አበው (አብርሃም: ይስሐቅና ያዕቆብ)
3.ቅዱስ እንድራኒቆስና ሚስቱ ቅድስት አትናስያ
4.ቅድስት ዓመተ ክርስቶስ
5.ቅዱስ ቴዎድሮስ ሮማዊ (ሰማዕት)

††† "እንግዲህ እግዚአብሔርን በመምሰልና በጭምትነት ሁሉ: ጸጥና ዝግ ብለን እንድንኖር: ልመናና ጸሎት: ምልጃም: ምስጋናም ስለ ሰዎች ሁሉ: ስለ ነገሥታትና መኳንንትም ሁሉ እንዲደረጉ ከሁሉ በፊት እመክራለሁ:: ሰዎች ሁሉ ሊድኑና እውነቱን ወደ ማወቅ ሊደርሱ በሚወድ በእግዚአብሔር በመድኃኒታችን ፊት መልካምና ደስ የሚያሰኝ ይህ ነው::" †††
(፩ጢሞ. ፪፥፩-፬)

††† ወስብሐት ለእግዚአብሔር †††
2024/06/01 16:23:23
Back to Top
HTML Embed Code: